Mols.gov.et

በአገር አቀፍ ደረጃ የአንተርፕርነርሺፕ ስልጠናን በወጥነት ለመስጠት የሚረዳ መመሪያ ርክክብ ተካሄደ

June 16, 2022
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኢንጆይ ኮንሰርቲየም አማካኝነት ያዘጋጀው መመሪያ የሥራ ዕድልን ለማስፋፋት ዋና መንገድ የሆነውን የአንተርፕርነርሺፕ ስልጠናን ወጥ በሆነ መንገድ ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ ኢንጆይ ኮንሰርቲየም የተዘጋጀውን መመሪያ ባስረከበበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር በከር ሻሌ (ዶ/ር) የህይወት ክህሎት እና የአንተርፕርነርሺፕ ስልጠና ወጣቶችን ከትምህርት ወደ ሥራ እንዲሸጋገሩ በማድረግ በኩል ትልቅ ጥቅም እንዳለው በመግለፅ የሚሰጡ ስልጠናዎችም ወጥ በሆነ ካሪኩለም እና መመሪያ መታገዛቸው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስልጠና መመሪያው ድግግሞሽን በማስወገድ ወጥ የሆነ ሥርዓት በመዘርጋት ለሥልጠና ሥርዓቱ የሚያበረክተው ሚና ትልቅ በመሆኑ ያዘጋጁትን ድርጅቶች እና ባለሙያዎች አመስግነዋል፡፡ የአንተርፕርነርሺፕ ፣ የሥራ ዝግጅት እና የህይወት ክህሎት ስልጠና መመሪያው በዋናነት ታላሚ ያደረገው የዩኒቨርሲቲ እና የቴክኒክና ሙያ ተማሪዎችን እንዲሁም ሥራ ፈጣሪዎችን በመሆኑ በርካታ ወጣቶች ላሏት ኢትዮጵያ ጠቃሚ መሆኑን የተናገሩት የካሪታዝ ስዊዘርላንድ የቀጠናው ዳይሬክተር የንስ ስትራንግል ናቸው፡፡ በአገሪቱ እየጨመረ ለመጣው የሥራ ፈጠራ ፣ ስልጠና እና አዎንታዊ የህይወት ለውጥ እንቅስቃሴ አስተዋፃኦ እንደሚያበረክት የተናገሩት በአውሮፓ ህብረት የግሪን ዲል ቡድን መሪ ዶሚኒክ ዳቮክስ እንዲህ ዓይነት መመሪያዎች ለውጥ የሚያመጣ ስልጠና ለመስጠት ያግዛሉ ብለዋል፡፡ በማንዋል ርክክብ ሥነስርዓቱ ላይ በአገሪቱ ስላለው የሥራ ዕድል እና ስልጠና ገለፃ የተደረገ ሲሆን መመሪያውን ያዘጋጀው ኢንጆይ ፕሮጀክት ሴቶች እና ወጣቶችን በተመለከተ ያከናወናቸውን ተግባራት አብራርቷል፡፡
en_USEN
Scroll to Top