በሲዳማ ክልል ክህሎት መር የሥራ ዕድል
October 14, 2025
በሲዳማ ክልል ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አብርሃም ማርሻሎ ገለፁ።
አቶ አብርሃም የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ባካሄደው የዘርፍ ጉባኤ እንደገለጹት ወጣቶች ተወዳዳሪ በመሆንና የተሻለ ሀብት በመፍጠር ረገድ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
የአካባቢን የልማት አቅም በመለየትና ወጣቶችን በቂ ክህሎት በማስጨበጥ እሴት በሚጨምሩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሚሆኑበት መደላድል የመፍጠር ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጉባኤው የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት እንደ ሀገር ብቁ የሰው ኃይል በማፍራትና ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
ክህሎት መር በሆነ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ እንዲሁም በተቋም ግንባታ ላይ የሪፎርም አጀንዳዎችን በመቅረጽ የተለያዩ ሥራዎች እተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በዚህም ላለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት በአማካይ በዓመት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በሲዳማ ክልል ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሀገረፅዮን አበበ ከ2015 ዓ.ም በፊት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው ክህሎትን ዋነኛ ትኩረት ያደረገ ባለመሆኑ በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት ሳይመዘገብ ቆይቷል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት አንድም ዜጋ ያለ በቂ ክህሎትና ሥልጠና ወደ ሥራ እንዳይገባ አቅጣጫ ተቀምጦ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
ይህም ቀደም ሲል የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ላይ ይስተዋል የነበረው የውጤት ማጣት፣ የመበተን፣ የመሰላቸትና ሀብት መፍጠር ያለመቻል ችግር ተፈትቶ ውጤት መታየት መጀመሩን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በመደበኛ ሥልጠና ከ30ሺህ በላይ እንዲሁም በአጫጭርና ገበያ ተኮር ሥልጠናዎች ከ61ሺህ በላይ ዜጎችን ማሰልጠን ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በሥልጠና ተቋማት፣ በአገልግሎት መስጫ እና በሥራ ማዕከላት ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥርዓትን በመዘርጋትም ዘርፉን የማዘመን ሥራ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በመድረኩ በተያዘው ዓመት በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማትና አጋር አካላት የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት መሰጠቱን የገለፀው ኤዜአ ነው።






