በማይታመን ፍጥነት በሁሉም ዘርፎች ውስጥ እየሰረፀ የሚገኘው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ
November 8, 2025
በማይታመን ፍጥነት በሁሉም ዘርፎች ውስጥ እየሰረፀ የሚገኘው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የጀመረውን አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስልጠና ለማስተዳደር በሚያስችሉ ህጎችና ደንቦች ዙሪያ ያተኮረ ጥናት ኢኒስቲትዩቱ በየሳምንቱ በሚካሄደው ጥናትና ምርምር ጉባኤ ላይ ቀርቧል፡፡
የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብታሙ ሙሉጌታ ዓለም በአሁኑ ጊዜ እያስተናገደች የምትገኘውን የዕውቀት፣ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ ያተኮሩ ውይይቶች በየሳምንቱ እየተካሄዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ኢኒስቲትውቱ አዳዲስ እና ጠቃሚ የጥናትና ምርምር ርዕሰ ጉዳዮችን በመዳሰስ በተቋሙ የጀመረውን ፈጣን የሆነ የሪፎርም ሥርዓት በውጤታማነት እንደሚያስቀጥልም ተናግረዋል፡፡
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ እያደገ የመጣ ቴክኖሎጂ ሲሆን በተለይም እንደ ኢንስቲትዩቱ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎች ዘርፉን ስርዓት ባለውና በኃላፊነትን በተላበሰ ስሜት ለመጠቀም በሚያስፈልጉ ህጎች፣ ደንቦችና ሥርዓቶች ላይ አተኩሮ ጉባኤው ተካሂዷል፡፡
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሥራን በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን ካለው ጠቀሜታ ባሻገር የሰው ልጅ ተጠቃሚነት ሳይጓደል ጎን ለጎን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለመሆን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከቀረበው የመነሻ ጥናት ላይ በመነሳት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ከቴክኖሎጂው አጠቃቀም ረገድ ሌሎች ሀገራት ያጋጠማቸው አይነት ችግር ሀገራችንን እንዳይገጥማት ተሞክሮዎቻቸውን በመቅሰም ከወዲሁ ውጤታማ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም በስፋት ተነስቷል፡፡
በዕለቱ በ‹‹በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም እንዴት የአየር ንብረት ብክለትን መቀነስ ቻላል ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡







