“በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚከናወኑ ተግባራት መዳረሻ ግባቸው ድህነትን በብልፅግና መርታት ነው።” ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
October 24, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ለመላ አመራርና እና ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
የሥልጠናውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚከናወኑ ተግባራት መዳረሻቸው ድህነትን በብልፅግና መርታትና ማሸነፍ በመሆኑ የአመራርና ሠራተኛውን አቅም ማላቅ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገርን የማፅናት ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችሉ በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን ቀርፆ ሲተገብር መቆየቱን ክብርት ሚኒስትሯ አስታውሰው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ስብራቶችን ከመጠገን ፣ የዜጎችን የመግዛት አቅም ከማሳደግ፣ ማህበራዊ ጠንቆችን ከማረምና፣ ዜጎችን በክህሎት አንፆ ወደ ሥራ ከማስገባት አንፃር የሚጠበቅብንን ተልዕኮ በብቃት ለመፈፀም ከመጣንበት መንገድ የፈጠነ እና የገዘፈ ሥራ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ‹‹ዓመተ ምርታማነት›› ተብሎ በተሰየመው የ2016 በጀት ዓመት ምርታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፈተሽና እውነተኛ ለውጥን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እንደሚከናወኑም አስረድተዋል፡፡
ዓመቱን እንደስያሜው ምርታማነት የሚረጋገጥበት እንዲሆን የተለየ አካሄድና ቁርጠኝነት መላበስ፣ በእውነተኛነትና በታማኝነት ማገልገልና በአገር ፍቅር ስሜት ኃላፊነትን መወጣት ከእያንዳንዱ አመራርና ፈፃሚ የሚጠበቅ ኃለፊነት መሆኑንም በአፅንዖት አሳስበዋል፡፡