Mols.gov.et

በሙያና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ዘላቂነት ላለው እድገት

May 24, 2023
ተማሪዎች በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ላይ እያሉ የተግባር ትምህርቶችን እንዲማሩ ማስቻል፣ እጃቸውን የሚያፍታቱበት፣ ክህሎትን የሚቀስሙበትን የትምህርት ዘዴ መከተል የትምህርት ስርዓቱን ሙያ ቀመስ (vocationalized) ማድረግ የሚያስችል አሰራር ነው፡፡ ወጣቶች በመደበኛ ትምህርት ላይ እያሉ የተለያዩ የሙያና የቴክኒክ ብቃቶችን በተግባር ሥልጠና ማግኘታቸው አንድም የአንዳች ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ እድል የሚፈጥርላቸው ሲሆን በሌላ በኩል የወጣቶች ሥልጠና የሚቀስሙበት የማድረግ፣ የመፈፀም፣ የማከናወንና ውጤትን የማስገኘት ልምምዳቸው በራስ መተማመናቸውን በእጅጉ እንደሚያሳድገው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የክህሎት ልማቱን በአገር አቀፍ ደረጃ እየመራ የሚገኘው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሙያና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ዘላቂነት ላለው እድገት ያለውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት በክህሎት የበለፀገ ዜጋን ለማፍራት ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል የመደበኛ ትምህርት ሥርዓት ሙያ ቀመስ እንዲሆን በማስቻል እጃቸው በሙያ የተፍታታ፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት አንዱ ነው፡፡ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለማውረድ እንዲቻልም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ለህፃናትና ታዳጊዎች የሙያ ስልጠናን ምንነትና ፋይዳ ማስረዳት ብሎም ለዘርፉ ፍቅር እንዲኖራቸው የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ማመቻቸት መደበኛ የትምህርት ሥርዓትን ሙያ ቀመስ (vocationalized) ለማድረግ ከሚሰሩ ሥራዎች አንዱ በመሆኑ ከግንቦት 14 እስከ 18/2015 ዓ.ም በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘውን 3ኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተማሪዎች እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ ተማሪዎቹ በጉብኝታቸው ወቅት በተመለከቷቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደተደነቁና በተለያዩ ዘርፎች ሲካሄዱ የተመለከቷቸው የክህሎት ውድድሮችም ትኩረታቸውን እንደሳቧቸው ተናግረዋል፡፡
Scroll to Top

The Ministry of Labor & Skills