Mols.gov.et

በልምድ የተገኘ ሙያን በምዘና በማረጋገጥ እውቅና መስጠት ስርዓቱ ይበልጥ አካታች እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ

January 6, 2025
በልምድ የተገኘ ሙያን በምዘና በማረጋገጥ እውቅና መስጠት ስርዓቱ ይበልጥ አካታች እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በልምድ የተገኘ ሙያን በምዘና በማረጋገጥ እውቅና መስጠት የዜጎችን ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ስርዓቱ አካታች እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተጠቆመ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ አንደገለጹት በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊን በላይ ዜጎች በመደበኛ ስልጠና ተደራሽ ይሆናሉ፡፡ በገበያ ተኮር አጫጭር ስልጠናም ከሦስት ሚሊየን በላይ ዜጎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ የሥራ ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ በአንፃሩ በርካታ ዜጎች ከመደበኛ ስልጠና ውጪ ባገኙት ሙያ የሥራ ገበያ ውስጥ ገብተው ይሰራሉ፣ ኢኮኖሚውንም በእጅጉ ይደግፋሉ፡፡ ነገር ግን በዚህ መልክ የሚገኝ እውቀትና ክህሎትን የሚያስተናግድ ስርዓት እስከ ቅርብ ጊዜ ስላልነበረን በልምድ የሙያ ባለቤት የሆኑ ዜጎች ተወዳዳሪነታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን በተገቢው ልክ ማሳደግ አይችሉን ነበር ብለዋል፡፡ ይህን ከግምት በማስገባትና የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ ሚኒስቴሩ በልምድ የተገኘ ሙያን በምዘና በማረጋገጥ እውቅና መስጠት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን አመላክተዋል፡፡ በርካታ ዜጎች በልምድ ያገኙትን ሙያ በመጠቀም በተለያዩ ዘርፎች በሥራ ላይ እንዳሉ ያመላከቱት ዶ/ር ተሻለ የኮንስትራክሽን፣ የቱሪዝምና የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ የተዘረጋው ስርዓት ይህን የሰው ሃይል ብቃቱን፣ ተወዳዳሪነቱ እና ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ወሳኝ ሚናም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የሥራ ጥራትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የሰው ሃይሉን ምርታማነት ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛም እንደሆነ ነው ዶ/ር ተሻለ ያመላከቱት፡፡ የተሻሻለ ሀገራዊ የሠራተኛ ፕሮፋይል እንዲኖረን፣ ማህበራዊ ትስስርን ከማጠናከር፣ የዕድሜ ልክ ትምህርትን ከማበረታታት እንዲሁም በትምህርትና ስልጠና ተቋማት እና በኢንዱስትሪው መካከል ጠንካራ ትብብር እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የተዘረጋው ስርዓት ሚናው የላቀ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡ ለሥርዓቱ ውጤታማነትም የዘርፉ ተዋንያኖች በሙሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉም ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top