ሚኒስቴሩ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ከሳውዲ አረቢያ የሰው ሃይል አስተዳዳር ተወካዮች ጋር ውይይት አካሄደ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ከተወካዮቹ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍ በኢትዮጵያ እና በሳውዲ አረቢያ መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ ስምምነት አተገባበርና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የዜጎችን መብት ደህንነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማው ባደረገው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ስልጠናና ምዘና ድረስ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ አብራርተዋል፡፡
ሥራውን ይበልጥ ለማዘመንና ከብልሹ አሰራር በማጽዳት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለሥራ ገበያው ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዴታው ከሳውዲ አረቢያ የሰው ሃይል አስተዳዳር ተወካዮች ጋር የተጀመረው ተቀራርቦ የመስራት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
የሳውዲ አረቢያ ተወካዮች በበኩላቸው እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አድንቀው ከመነሻ እስከ መዳረሻ ድረስ ያለውን ሂደት ጤናማ በማድረግ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡