Mols.gov.et

ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጅምር ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራ ፣ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ

November 8, 2024
ሚኒስቴሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጅምር ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው፡፡ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራ ፣ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (ILO) የጋራ ትብብር የተዘጋጀው ውጤታማ የሥራ ላይ ልምምድ እና ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄዷል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሥራ ፈላጊዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ ተግባራዊ ክህሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ የአሰራር ሥርዓትን ለመዘርጋት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በዚህም መሰረት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ቀደም ብሎ የሥራ ላይ ልምምድ መመሪያ ማፅደቁን የገለፁት ክቡር አቶ ሰለሞን ይህ መመሪያ በዓለም የሥራ ድርጅት የሥራ ላይ ልምምድ ጥራትን አስመልክቶ ካስቀመጠው ምክረ ሃሳብ ጋር ተናባቢ መሆን እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡ ይህ ተናባቢነት የሥራ ልምምዱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ለተለማማጅ ሰልጣኞች እሴት አካይ የሆነ ልምድ እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በመድረኩ የዓለም የሥራ ድርጅት ከአሠሪዎች ፌዴሬሽንና ከመንግስት ጋር በመተባበር ‹‹ፕሮ አግሮ›› በተሰኘው ፕሮጀክቱ በዶሮ እርባታ ዘርፍ 200 የሚሆኑ ወጣቶች እንዲሁም ‹‹ፕሮስፔክት›› በተሰኘው ፕሮግራሙ በብየዳና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዘርፍ 300 የሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ የሥራ ገበያው በሚፈልገው ደረጃ ሰልጣኞችን ለማብቃት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን መደገፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሂደት መሆኑን የጠቀሱት ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ሚኒስትር መ/ቤቱ በዚህ ዙሪያ የተሠማሩ አካላትን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ በመድረኩ የዓለም የሥራ ድርጅት፣ የኢኖቬሽንነና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአይ ሲ ቲ ፓርክ፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ እና አጋር አካላት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top