መንግሥት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትኩረት ሰጥቷል – የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር..
August 9, 2025
መንግሥት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትኩረት ሰጥቷል – የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
መንግሥት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትኩረት መስጠቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ገለጹ።
በኮሪያ ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ ድርጅት(ኮይካ) እና በኤልጂ ኤሌክትሮኒክስ ድጋፍ የተቋቋመው ኤልጂ ኮይካ ሆፕ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለሁለት ዓመታት ያሰለጠናቸውን ከ70 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተገኙት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) መንግስት ለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ውጤታማነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ከ1ሺህ 500 በላይ የመንግስትና የግል ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዳሉ ጠቅሰው የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ ድርሻቸው የላቀ ነው ብለዋል።
በየአመቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች አጫጭር ስልጠዎችን እንዲሁም ከግማሽ ሚሊየን በላይ ዜጎች ደግሞ የረጅም ጊዜ ስልጠና እንደሚወስዱ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
በዘርፉ ስልጠና ወስደው የሚመረቁ ወጣቶች የራሳቸውን የስራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው በሚገኙ የልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ትልቅ አቅም እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ኮሌጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወጣቶች በቀላሉ ገበያ ውስጥ ገብተው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ተመራቂዎቹ በንድፈ ሃሳብ የቀሰሙትን ትምህርት ወደ ተግባር በመቀየር ሀገራቸውን የሚጠቅም ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ በበኩላቸው፥ ኮሌጁ በርካታ ወጣቶችን ያለምንም ክፍያ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች እያሰለጠነ ይገኛል ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ እና በኮሪያ ሪፐብልክ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ተማሪዎች የቀሰሙትን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ወደ ተግባር በመቀየር ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ስራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኮሌጁ ኃላፊ ታሪኩ አበበ እንዳሉት ኮሌጁ በኤሌክትሮኒክስ ኮሙኒኬሽን፣ መልቲሚዲያ፣ የቤትና የቢሮ እቃዎች መገጣጠም፣ የአይሲቲ ሀርድዌር እና ኔትወርኪንግ ፕሮግራሞች ለሀገር ውስጥና ከውጭ ለመጡ ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ስልጠናውን የወሰዱ ተማሪዎች ስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የሚደረግ መሆኑንና ለውጤታማነቱም ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲሚደረግላቸው ጠቅሰዋል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያስመረቃቸው ተማሪዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የስራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ተናግረዋል።
ኮሌጁ የዛሬውን ጨምሮ በእስካሁኑ ቆይታው በአጠቃላይ ከ1ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች ማስመረቁንም አንስተዋል።
በዛሬው እለት ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል የማዕረግ ተመራቂ የሆነው አዶንያስ ዘውዴ ሀገርን ለመደገፍ ራስን ብቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል።
በተለይም ለሽልማት ያበቃው ፕሮጀክት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚሰራው ስራ ውስጥ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ ለሀገሬ የድርሻዮን እወጣለሁ ነው ያለው።
ሌላኛዋ የማዕረግ ተመራቂ ሃያት አብደላ በበኩሏ ያስመዘገበችውን ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ሙሉ ጊዜዋን ለጥናት በመስጠት በርትታ መስራቷን ተናግራለች።
በዚህም በተመረቀችበት ዘርፍ ሀገሯን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗንም ጨምራ ገልጻለች።
በዶሮ እርባታ ዘርፍ ከሰዎች ንክኪ ነጻ የሆነ ማሽን በፕሮጀክት መልክ መስራቱን ጠቅሶ ይህንን ማሽን በስፋት በማምረት በዘርፉ ላይ የድርሻውን እንደሚወጣ የተናገረው ደግሞ ሌላኛው ተመራቂ አልአዛር መስፍን ነው። ዘገባው የኢዜአ ነው






