Mols.gov.et

‹‹ ለኢንተርፕሪነሮች፣ ክፍት ይሁኑ በሮች! ››

December 8, 2023
‹‹ ለኢንተርፕሪነሮች፣ ክፍት ይሁኑ በሮች! ›› የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የዓለም አቀፉን የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ከህዳር 24/2016 ዓ.ም ጀምሮ እያከበረ ይገኛል፡፡ ‹‹ለኢንተርፕሪነሮች፣ ክፍት ይሁኑ በሮች›› በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ በሚገኘው በዚህ በዓል ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የሥራ ዕድልን የሚያሰፉና አዳዲስ የፈጠራና የኢኖቬሽን ሃሳቦች በልፅገው ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የሚያስችሉ ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ‹‹ከህዳር እስከ ህዳር›› በሚል ኢንትርፕሪነርሺፕን ለማበልፀግ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን የጠቀሱት ክብርት ሚኒስትር የፈጠራ ሃሳብ ውድድሮችን በማድረግ ኢኖቬተሮችን የማበረታታትና የማብቃት ሥራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በዓመቱ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ እያንዳንዱ ወረዳዎች የተውጣጡ ከአንድ ሺ በላይ ተወዳዳሪዎችን ያሳተፈ አገር አቀፍ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ማካሄድ መቻሉንም ክብርት ሚኒስቴር ተናግረዋል፡፡ በዓመቱ በተካሄዱ ውድድሮች አሻናፊ የሆኑ ወጣቶችንና ሌሎችም የፈጠራና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ሃሳብ ወደ ምርት ለመቀየር እንዲቻልም ‹‹የሠመር ካምፕ›› በሚል ሥያሜ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው ፕሮጀክት የፈጠራ ባለሙያዎቹ በአንድ ማዕከል ተሰባስበው በሚደረግላቸው የቴክኖሎጂና የባለሙያ እገዛ የፈጠራ ሃሳባቸውን የማበልፀግና የማሳደግ ሥራ እየሰሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡ የኢንተርፕሪነርሺፕ እሳቤ እንዲዳብርና ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው ለማስቻልም ለሥራና ክህሎት ተጠሪ የሆነውን የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩትን የማጠናከር ተግባር መከናወኑም ተገልጿል፡፡ የኢንተርፕሪነርሺፕ ምህዳርን ለማስፋት የተጀመሩ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያስረዱት ክብርት ሚኒስትር ‹‹ለኢንተርፕሪነሮች፣ ክፍት ይሁኑ በሮች፤ ›› የሚለውን መሪ ሃሳብ ለመተግበር በሚያስችል መልኩ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ ግፊት ማድረግን ጨምሮ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን የማጠናከር ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን የማስፋትና የፈጠራ ባለቤቶችን የማብቃት ሥራ በስፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top