ሁሉም ሲያሸንፍ ሀገር ትቀናለች!
April 28, 2024
ሁሉም ሲያሸንፍ ሀገር ትቀናለች!
ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ላለፉት ሶስት ሳምንታት ሲካሄድ የሰነበተው የስታርትአፕ ኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎችና የአዳዲስ ግኝቶች ባለቤቶች የውድድር መድረክ ተጠናቀቀ፡፡
በዚህ የስታርትአፕ ኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎችና የአዳዲስ ግኝቶች ባለቤቶች የውድድር መድረክ እና አውደ ርዕይ ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት
ሁሉም ተሳታፊዎች አሸናፊ በሆኑበት ላለፉት ሶስት ሳምንታት ሲካሄድ የሰነበተው የስታርትአፕ ኢትዮጵያ የሥራ ፈጣሪዎችና
የአዳዲስ ግኝቶች ባለቤቶች የውድድር መድረክ እና አውደ ርዕይ ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ የሀገር ተስፋ የሆኑትን ብርቅዬ ወጣቶች የማበረታታት እድል በማግኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል! ተሸላሚዎች እንኳን ደስ ያላችሁ! ብለዋል፡፡
አክለውም ስታርትአፖች በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ በሚጫወቱት ወሳኝ ሚና ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ብልፅግና አንቀሳቃሽ ሞተር ናቸው:: አዳዲስ ሀሳቦችን እና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ምርታማነትንና የስራ ዕድል ፈጠራን ያስፋፋሉ:: ከአዳዲስ የገበያ ፍላጎቶች ጋር ለመላመድ ያላቸው ቅልጥፍና እና ብቃታቸው ኢንዱስትሪዎችን እንዲጎለብቱ እና አዳዲስ ምርቶችን እንዲፈጥሩም ያስችላሉ::
ይህ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን አመራርና አነሳሽነት እንዲሁም በሰባት ተቋማት ትብብር (የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢንተርፕሩነርሺፕ ልማት ኢንስቲቲዩት እና የገበያ ባለስልጣን) በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው አዳዲስ የፈጠራ ሀሳብና እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዘው የቀረቡ ወጣቶች ልምዳቸውን የተለዋወጡበት ስታርትአፖች የመተዋወቅ እድል ያገኙበት ውጤታማ ስራ ፈጣሪነት የተበረታታበትና የፈጠራ ስራዎች እንዲጎለብቱ ምቹ ምህዳር የተፈጠረበት መርሃ ግብር ነበር:: ሥለሆነም ስታርትአፖች ይህንን የተፈጠረ ምቹ መደላድል ተጠቅማችሁ የላቀ ውጤት እንደምታስመዘግቡ ሙሉ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡