ሁለተኛው የአፍሪካ የሰው ሃብት ልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
October 2, 2023
ለሰው ሀይል ልማትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች ምቹ ሥነ-ምህዳር መፍጠር የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮች እና የሲቪል ማህበራትን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል።
ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
ሁለተኛው የአፍሪካ የሰው ሃብት ልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው “ራስን የሚደግፍ ሥነ-ምህዳር መገንባት፤ የቀጣይ ሥራ የሚፈልገው ክህሎት፣ የክህሎት ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እተካሄደ የሚገኘው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፣ የሥራው ዓለም በፍጥነት እየተቀያየረ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየመጡ እና የዓለም ኢኮኖሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሳሰረ መጥቷል፡፡
ታዲያ እነዚህ ለውጦች ለሠራተኞች አዳዲስ እድሎችን እንደመፍጠራቸው አዳዲስ ፈተናዎችን ይዘው መምጣታቸው አልቀረም፡፡
በዚህም በቴክኖሎጂና ፈጠራ ዙሪያ የተከሰቱት ግዙፍ ለውጦች ሀገራት በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ያሉ የክህሎት ፍላጎት፣ ዓይነቶችን እና ደረጃዎቻቸው እንዲጨምሩ እያደረገ ይገኛል፡፡
የአፍሪ አጀንዳ 2063 ይህን ከግምት ያስገባ ሰሆን በሀገራችንም በአስር ዓመቱ የልመት ዕቅድና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሰው ሀብት ልማትና ሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶች በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል ብለዋል፡፡
የሀገራችን የሥራ ገበያ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ነው ክቡር ሚኒስትሩ ያመላከቱት፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከክህሎት ልማቱ በተጨማሪ የተግባር ልምምድ እና የሥራ ላይ ስልጠና ወሳኝ ስትራቴጂ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሀገር እየተደረገ ያለው ጥረት የተቀናጀ፣ ራሱን የቻለ እና ፍላጎት መር ክህሎት፣ ሥራ ዕድል እና ለሥራ ምቹ የሆነ ስነ-ምህዳር መፍጠር ነው እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር በለጠ ይህም የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮች እና የሲቪል ማህበረሰብን ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመቅረጽ እና ፍላጎት መር የክህሎት ስልጠና እና ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆኑ በዚህ ዙሪያ በትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባም ነው ዶ/ር በለጠ ያሳሰቡት፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው፣ ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስነ-ምህዳር መፍጠር የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪክ ማህበራትን ቅንጅትና ትብብር ይጠይቃል።
ይህን ማድረግ ሲቻል እምቅ የመልማት አቅሞቻችንን በማውጣት ሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ያለው ዕድገት አስተዋፅዖ የሚያደርግ የክህሎት ልማት ስነ-ምህዳር መገንባት ይቻላል ብለዋል፡፡