Mols.gov.et

ቢሮው የISO 9001:2015 ትግበራን በይፋ ጀመረ

April 30, 2026
ቢሮው የISO 9001:2015 ትግበራን በይፋ ጀመረ የአማራ ክልል የሥራና ክህሎት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጡን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችለውን የቴክኒክ ድጋፍ ስምምነት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር ተፈራርሟል። ስምምነቱን የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ስቡህ ገበያው እና የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት በቀለ ፈርመዋል። በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ዶ/ር መሰረት በቀለ እንደገለጹት፣ የጥራት ማኔጅመንት ሥርዓትን መተግበር ተቋማት የተገልጋይ እርካታን በተጨባጭ እንዲያረጋግጡ ከመርዳቱም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ስምምነቱ ቢሮው ከክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች አኳያ የሚሰጠውን አገልግሎት ምቹ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችለው ተመላክቷል። ቢሮው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በስሩ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በጀመረው ጥረት፣ በ2017 በጀት ዓመት 5 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የISO ትግበራን አጠናቅቀው እውቅና ማግኘት ችለዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም ተጨማሪ 7 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችን የጥራት ሥራ አመራር ስርዓት ማረጋገጫ ባለቤት ለማድረግ ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መገባቱ ቢሮው አስታውቋል።
tigTIG
Scroll to Top