ስምምነቱ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር፤ ስምምነቱ ኢንስቲትዩቱ ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን በማሻሻል በኩል ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰራ ዕድል የሚፈጥርና በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች በኢንስቲትዩቱ እንደሚሰሩም አመላክተዋል።
ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ችግር ፈቺ የሆኑ ተኪ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራት በትኩረት እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ የቡና ጥራትን በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የክህሎት ስልጠናዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ካለው የማሰልጠን፣ የፈጠራ እና የምርምር ሥራዎች አቅም አንጻር አብሮ መስራቱ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ነው ያመላከቱት። መረጃው የኢኒስቲትዪቱ ነው።