Mols.gov.et

ፈጠራና ፍጥነትን ማዕከል አድርጎ ተኪ ምርት ማምረት…

May 8, 2026
ፈጠራና ፍጥነትን ማዕከል አድርጎ ተኪ ምርት ማምረት ለኢኮኖሚ ሽግግሩ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን በፈጠራና በፍጥነት በማሳደግ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የኢኮኖሚ እድገቱን ማፋጠን እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለጹ። አፈ-ጉባኤዋ ይህንን የገለፁት በሸገር ከተማ ገላን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተጀመረውን የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የፈጠራና የክህሎት ውድድርን ባስጀመሩበት ወቅት ነው። የተከበሩ ወ/ሮ ሰዓዳ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፤ መንግስት በትምህርት፣ በሙያ ስልጠና እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች ውጤት እያሳዩ ይገኛሉ። በተለይም በየዓመቱ የሚፈጠሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሥራ ባህልን በመቀየር ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህ ፈጠራዎች የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የስልጠና ተቋማትም የገበያ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ጥናት በማድረግና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸውን ትብብር በማጠናከር፤ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት እንዳለባቸው ተገልጿል። ይህም የኢኮኖሚ ሽግግሩን ከማሳለጡ ባለፈ ሀገር በቀል ዕውቀትን ወደ ምርት በመለወጥ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል። የኦሮሚያ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ጎልጋ በበኩላቸው፤ ቢሮው ሰፊ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንንም ግብ ለማሳካት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የክህሎት ማዳበሪያና ዘላቂነት ያላቸው ስልጠናዎች በስፋት እየተሰጡ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። በ22 ክላስተሮች እና በ215 የስልጠና ተቋማት መካከል የሚካሄደው ይህ ውድድር፤ የሸገር ከተማን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው እቅድ ስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመድረኩ መገለፁን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
tigTIG
Scroll to Top