Mols.gov.et

5ኛው ዙር ክልላዊ የቴክኖሎጂና ተግባራዊ ምርምር ውድድር ተጠናቀቀ

May 8, 2026
5ኛው ዙር ክልላዊ የቴክኖሎጂና ተግባራዊ ምርምር ውድድር ተጠናቀቀ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት የ5ኛው ዙር ክልላዊ የቴክኖሎጂና ተግባራዊ የጥናትና ምርምር ውድድር ተጠናቋል፡፡ ውድድሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪና ከክልል መንግሥታት ጋር ያላቸውን ትስስር ለማጠናከርና የምርምር ውጤቶች በቀጥታ ወደ ማህበረሰቡ የሚወርዱበትን ዕድል ለመፍጠር ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት አድርጎ የተካሄደ ነው፡፡ በዳኞች ግምገማና በድምር ውጤት መሠረት፣ የአሶሳ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እና የቡለን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በአንደኝነት በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ደግሞ የሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ ቢሮው ለአሸናፊዎቹ እንደየደረጃቸው ከ15ሺህ እስከ 25ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ማበረታቻና የዕውቅና ምስክር ወረቀት በማበርከት ኮሌጆቹ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በጥናትና ምርምር ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ አበረታቷል፡፡ የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱሰላም ሸንገል በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ ቴክኖሎጂ ለሀገርና ለክልል ልማት የማይተካ ሚና አለው፡፡ እንዲህ ያሉ ውድድሮች በወጣቶችና በተመራማሪዎች ዘንድ የፈጠራ ባህልን ለማዳበር እና ተግባራዊ ምርምሮችን ወደ ምርታማነት ለመቀየር ወሳኝ መድረኮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ይህን ውጤታማ ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው አረጋግጠዋል። በተለይም አሶሳ ግብርና ኮሌጅ በአንደኝነት እንዲያሸንፍ ያስቻለው “Improving organic farming practice by using vertical farming” በሚል ርዕስ ያቀረበውና በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ያለመው የምርምር ሥራ በዳኞች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል፡፡ ተመራማሪዎቹና የኮሌጁ አመራሮች በበኩላቸው የተገኙ ውጤቶችን ወደ ማህበረሰቡ የማሸጋገርና በሀገር አቀፍ ደረጃም የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ ዘገባው የቤኒሽንጉል ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ነው
tigTIG
Scroll to Top