‹‹የአፍረካ ክህሎት ልማት ስትራቴጂ CTVET 2025- 34 ››
October 15, 2025
‹‹የአፍረካ ክህሎት ልማት ስትራቴጂ CTVET 2025- 34 ››
ከጥቅምት 3- 7/2018 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት ዋና መ/ቤት እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የክህሎት ልማትን በአፍሪካ ለማስፋት የተዘጋጀው ‹‹የአፍረካ ክህሎት ልማት ስትራቴጂ (CTVET) 2025- 34 ›› የማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
የስትራቴጂውን ተግባራዊነት አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት ሰነዱ ቀጣይነት ያለው እድገትና ማህበራዊ ፍትህ በአህጉሪቱ ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ያለውን እምቅ አቅም በጥቅም ላይ ለማዋል የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የስትራቴጂው መዘጋጀት አፍሪካውያን በተለይም ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎችም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜው የሚፈልገውን ክህሎት እንዲላበሱ ብሎም የሥራውን ዓለም በስፋት እንዲቀላቀሉ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
ስትራቴጂው ከ’አጀንዳ 2063′ እና ‘ከተባበሩት መንግስታት የልማት ግቦች’ ጋር በማጣጣም አካታችነትን፣ እኩል ተጠቃሚነትን እና ኢኖቬሽንን መሰረት ያደረገ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተቀርጿል፡፡
በመሆንም የሀገራት ፖሊሲ፣ አስተዳደር፣ የፋይናንስ ስርዓት፣ ጥራትና አካታችነት ፣ አጋርነት፣ ዕውቀትና ሀብትን መጋራት በስትራቴጂው ውስጥ ልዩ ትኩረትየተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ፣ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ስትራቴጂውን ወደ ሥራ ከማስገባት ረገድ የየድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ተገልጿል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሥርዓትን በማሳደግ ዜጎችን ተገቢውን ክህሎት ማላበስ መጪው ጊዜ ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመልካም ዕድልና ተስፋ የተሞላ እንዲሆን የሚያስችል ቁልፍ አጀንዳ መሆኑም በውይይቱ ላይ በአፅንኦት ተነስቷል፡፡






