Mols.gov.et

የሥራ ባህል ግንባታ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት

April 8, 2026
የሥራ ባህል ግንባታ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን የኩባንያዎች መፈልፈያ ለማድረግ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተቀረፀውን አዲሱን የሪፎርም እሳቤ መነሻ በማድረግ በርካታ የሥልጠና ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን እያቋቋሙ ይገኛሉ፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ሰልጣኞች ተግባራዊ ሥልጠናን በተጨባጭ የሚያገኙባቸው እንደመሆናቸው ጠንካራ የሥራ ባህል ከማዳበር አንፃርም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የሥራ ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ሸዋቀና ወልደ አማኑኤል እንደሚያብራሩት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ የሚሳተፉ ሰልጣኞች የጊዜ አጠቃቀምን፣ ሥራን በአግባቡ መፈፀምን፣ እንዲሁም ኃላፊነትና ተጠያቂነትን በተግባር ይለማመዳሉ። ይህም በሥራ ቦታ የሚፈለገውን የዳበረ ሥነ-ምግባር እንዲያጎለብቱ ከመርዳቱም በላይ በቡድን የመስራት፣ የመግባባትና የመተባበር ክህሎታቸው እንዲያድግ ያደርጋል። እነዚህ እሴቶች ሰልጣኞች ወደፊት ወደ ሥራው ዓለም ሲሰማሩ በቀላሉ እንዲላመዱና ውጤታማ እንዲሆኑ መሰረት ይጥላሉ። በተጨማሪም በተቋማቱ ውስጥ የሚቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች የሰልጣኞችን የኢንተርፕርነርሽፕ አስተሳሰብ (Entrepreneurial mindset) በማሳደግ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አቶ ሸዋቀና ገልጸዋል። ሰልጣኞች የገቢና ወጪ ቁጥጥርን እንዲሁም የገበያ ትስስርን በተግባር እንዲያውቁ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠር ያላቸውን ተነሳሽነትና በራስ መተማመን ይጨምራል። ይህም ጥራትን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ላይ በማተኮር በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የመሆን አቅምን ይፈጥርላቸዋል። ባጠቃላይ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ሰልጣኞችን ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ ለተግባራዊ ዓለም የሚያዘጋጅ ስትራቴጂ ነው። ይህ አሰራር ሰልጣኞች በሙያዊ ክህሎት የበለፀጉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና የሥራ ዲሲፕሊን የተላበሱ እንዲሆኑ በማድረግ ወደ ሥራ ገበያው ሲገቡ የተሻለ ተመራጭነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መሪ ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡
tigTIG
Scroll to Top