Mols.gov.et

የህዝብ አገልግሎቱን ፈጠራን ማዕከል ያደረገና መፍትሄ አመንጪ እንዲሆን ማስቻል

December 16, 2025
የህዝብ አገልግሎቱን ፈጠራን ማዕከል ያደረገና መፍትሄ አመንጪ እንዲሆን ማስቻል እንደ ሀገር ምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት የህዝብ አገልግሎትን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ከብልሹ አሠራሮች የፀዳ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ይህን መሰሉን የአሠራር ማሻሻያ ዕውን ለማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት የህዝብ አገልግሎት የፈጠራ ማዕከል (public sector innovation lab) በሚል ስያሜ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ፈጠራን፣ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅና አዳዲስ ሃሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት ያለመውን የዚህን ሥርዓት ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ግንባታን ጨምሮ የአሠራር ሥርዓት የመዘርጋትና ተገቢውን መዋቅር የማደራጀት ሥራ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከየሥራ ክፍሉ ለተውጣጡ የተለያዩ ባለሙያዎች በቀጣይ አሠራሩን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የስልጠናው ዋና አላማ በሚቀጥሉት አመታት ውስጥ 500 ችግር ፈቺና መፍትሔ አመንጪ የህዝብ አገልግሎት ፈጣሪ አሸናፊዎችን መፍጠር ነው፡፡ ለአንድ ወር የሚቆየውን ይህ ስልጠና በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት የህዝብ አገልግሎት ፈጠራን በተመለከቱ እሳቤዎች (በ system thinking, feature thinking, design thinking, እና innovation ላይ) በማተኮር ይሰጣል፡፡ በቀሩት ቀናቶች ሰልጣኞች በየሥራ ክፍላቸው ውስጥ በተጨባጭ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንዲለዩና ፈጠራ በታከለበት መልኩ መፍትሔዎችን እንዲያመነጩ ይጠበቃል፡፡ የቀረጿቸው የመፍትሔ ሃሳቦች ከተመዘኑና ከተገመገሙ በኋላም የሃሳቡ ባለቤቶች የምስክር ወረቀት ባለቤት እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡ ስልጠናው በቀጣይም ለክልሎች፣ ለዞኖች፣ ለፌዴራል እና ለተጠሪ ተቋማት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
tigTIG
Scroll to Top