Mols.gov.et

በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ተዘጋጅተው በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ሥራ የጀመሩት የመስኖ መቆጣጠሪያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ግብርናን ለማዘመን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸው ተገለጸ።

July 29, 2025
በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ተዘጋጅተው በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ሥራ የጀመሩት የመስኖ መቆጣጠሪያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ግብርናን ለማዘመን ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸው ተገለጸ። በኢንስቲትዩቱ የክህሎት ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮግራም የተዘጋጁ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ሥራ ማስጀመሪያና የርክክብ መርሃ ግብር በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ሸበሌይ ወረዳ ሆረሀውድ ቀበሌ ተከናውኗል። ከቴክኖሎጂዎቹ መካከል በተለይም የመስኖ አውታርን መጠቀም የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ እና የከሰል ማክሰያ ቴክኖሎጂዎች ይጠቀሳሉ። በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀዳለ ተክሉ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ፈጣን የሪፎርም ሥራዎች እንዲሳኩ በየዘርፉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና ወደ ሥራ ማስገባት ወሳኝ ሚና አለው። ቴክኖሎጂው የተሰናዳው “እስኪል ኢትዮጵያ” በሚል ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ልጆችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣትና ስልጠና በመስጠት ነው ብለዋል። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቴክኖሎጂን የመስራትና የማሸጋገር ተልዕኳቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ማሳያ መሆኑንና ቴክኖሎጂውን ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል። የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ኢንስቲትዩቱ በጋራ የጀመሩት ይሄው የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ፕሮግራም በተለያዩ ዘርፎች ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን በማበልጸግ ለችግሮች መፍትሄ እያመጡ እንደሚገኙም አንስተዋል። ይህንን ቴክኖሎጂ በመጀመሪያው ዙር በክህሎት ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ የተሳተፉ ወጣቶች የተሠራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናገረዋል። ቴክኖሎጂውን በሀገር አቀፍ ደረጃ በማስፋትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በሁሉም ዘንድ በማላመድ በተለይም ግብርናውን ይበልጥ ለማዘመን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል። የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድርያስ ጌታ(ዶ/ር)፤ በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጁ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች በሶማሌ እና አፋር ክልሎች እንደተጀመሩ ገልጸው፤ በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት ምርትን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ቴክኖሎጂ ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የተጀመሩ የግብርና መስኖ ለየት የሚያድረገው የትም ሆነው ኢንተርኔትን በመጠቀም ማዘዝና መቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነ ገልጸው በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ተግባራዊ የተደረገ ነው ብለዋል። በቴክኖሎጂው የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል አቶ መሀመድ አህመድ፤ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ የልማት ሥራን ወደ ሌሎችም አካባቢዎች እንዲያሰፋ ጠይቀዋል። በመርሀ ግብሩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ሃላፊዎች፣ የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውን ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።
tigTIG
Scroll to Top