በልምድ የተገኘ ሙያን መዝኖ ዕውቅና መስጠት
4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር አምስተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡ በዛሬው ዕለትም የውድድሩ መርሃግብር የሆነው ‹‹በልምድ የተገኘ ሙያን መዝኖ ዕውቅና መስጠት›› በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የፓናል ውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ‹‹አንድ ሙያ ለአንድ ዜጋ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውና ዜጎችን የሙያ ባለቤት የማድረግ ዓላማ ያለው ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
ዜጎችን የሙያ ባለቤት ለማድረግ የተያዘው ይህ ዕቅድ በመደበኛ የሙያ ስልጠና ብቻ ይሳካል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በመሆኑም በልምድ የሙያ ባለቤት የሆኑ ሰዎችን መዝኖና ብቃታቸውን አረጋግጦ ዕውቅና ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡
ፕሮግራሙ ላይ በማተኮር እየተካሄደ ያለው የፓናል ውይይት በልምድ የሙያ ባለቤት የሆኑ ሰዎችን መዝኖና ብቃታቸውን አረጋግጦ ዕውቅና መስጠት ጠቀሜታ፣ በትግበራ ወቅት ባጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ እንደሚያተኩር በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡