Mols.gov.et

የኮደርስ ስልጠና ዜጎች በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል- የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

September 28, 2024
የኮደርስ ስልጠና ዜጎች በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል- የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ”አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርኃ ግብር የዜጎችን አቅም በማሳደግ በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ”አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትብብር የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣በአንድሮይድ ማበልፀግ ፣ በዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው። ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የ”አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ ኢኒሼቲቭ የዜጎችን የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነት አቅም የሚያሳድግ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ ዜጎች የዲጂታል ክህሎት በመጨበጥ ስራ እና ሀብትን በመፍጠር ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን የበለጠ የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል። በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶችን ከማፍራት አንጻር የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል። በዚህ ሂደት የሚያልፉ ዜጎች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ከማብቃት በተጨማሪ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶችን ማፍለቅ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት። ስልጠናው በሌላው ዓለም ያሉ ስራዎችን ባሉበት ሆነው መስራት እንዲችሉ የሚያግዝ ነው ብለዋል። ከዚህም ባለፈ የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለሀገር ለማበርከት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ሲሉ አመላክተዋል። ይህም የዜጎችን የተወዳዳሪነት አቅም በማሳደግ በዲጂታሉ ዓለም ባለው የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛል ነው ያሉት። መርኃ ግብሩ በፈረንጆቹ በ2026 አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታሳይንስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት የሚያስጨብጥ ይሆናል። #ኢዜአ መስከረም 18/2017
tigTIG
Scroll to Top