የሥራ ጉባዔ ዓለማቀፍ እንዲሆን እንመኛለን፤ እናሳካዋለንም
July 9, 2023
የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በጋራ ባዘጋጁት የአፍሪካ የመጀመሪያው የሥራ ጉባዔ የዕውቅና ሽልማት መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የኢፌዲሪ ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ኢንተርፕራይዞች እና የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ዕውቅናና ሽልማት አበረክተዋል።
ክቡር ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ በ2014 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች፣ የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ 3 ቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች እና ወደ ታዳጊ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የሜዳሊያ እና ምስክር ወረቀት ካበረከቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር አዘጋጆቹን አመስግነዋል።
በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረው የሥራ ጉባዔ አድጎ በአፍሪካ ደረጃ ለመካሄድ በቅቷል በማለትም ዓለማቀፍ ሆኖ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው ፎረም እንዲሆን እንመኛለን እናሳካዋለን ሲሉም ተናግረዋል።
ዕውቅና ለተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞችም ለሽልማት መብቃት ትልቅ ስኬት ነው ካሉ በኋላ አሁንም ብዙ መጣር እና ለላቀ ስኬት መጓዝ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
የሥራ ዕድል መፍጠር ለአፍሪካ እንደ አህጉር እና ለኢትዮጵያም ብዙ ኃላፊነት የሚጠይቅ ወቅታዊ አጀንዳ ነው በማለት ከተሠራው ያልተሠራው ይበልጣል፤ ላልተሠራው ፀንተን እንራመድ ሲሉ ተናግረዋል።