Mols.gov.et

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን አበልፅጎ ወደ ሥራ ማስገባቱ ለሥራ የሚደረግ ፍልሰትን ለማስተዳደር የሚያስችል አገራዊ አቅም ፈጥሯል፡፡ ክቡር አሰግድ ጌታቸው(ዶ/ር) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ

October 9, 2023
የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓት ላይ በማተኮር የተካሄደውን የውይይት መድረክ በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አሰግድ ጌታቸው(ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ለሥራ ፍለጋ የሚደረግ ፍልሰት በአግባቡ ከተመራ የፍልሰተኞችን የትውልድም ሆነ መዳረሻ አገራትን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍልሰተኞች ጋር ተያይዘው በመነሻ ፣ በመሸጋገሪያ እና በመዳረሻ አገራት ላይ የሚያጋጥሙ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች ፍልሰተኞችን ከመፈተን አልፈው ህይወታቸውን አደጋ ላይ እስከመጣል እንደሚደርሱም ሚኒስትር ዴኤታው በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም መሰል ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች፣ ምክክሮች፣ ቅንጅቶችና ትብብሮች በአገር እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአገሪቱ ምቹ የሥራ ሁኔታን ከማመቻቸት እና ለሥራ የሚደረግ ፍልሰትን ከማስተዳደር አንፃር ጉልህ ድርሻ ያለውን የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን አበልፅጎ ወደ ሥራ ማስገባቱ በዘርፉ ልዩ አቅምን ለመፍጠር እንዳስቻለም ክቡር ዶ/ር አሰግድ በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የተደረገው ጥረት ለሥራ ከአገር ውጪ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ይስተዋል የነበረውን የዜጎች እንግልት ያስቀረ ከመሆኑም በላይ ከመዳረሻ አገራት ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑ በዘርፉ የጎላ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉም ተገልጿል፡፡ የፍልሰት አስተዳደር ሥርዓትን ከማዘመን፣ ከሥራ ፍልሰት ጋር ተያይዞ አገራት የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ከማስቀመጥ፣ በአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙ አገራት ዜጎች በቀጠናው ውስጥ የሥራ ዕድሎችን ከማመቻቸት እና ህገወጥ ስደትን ከመግታት አንፃር ጉልህ ሚና ያለው የቴክኒክ ቡድን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን፣ የዓለም የሥራ ድርጅትንና ሌሎችንም አጋር አካላትን አካቶ መቋቋሙን የገለፁት ክቡር ዶ/ር አሰግድ ጌታቸው ቡድኑ ያዘጋጀው ዕቅድ በመድረኩ ፀድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
tigTIG
Scroll to Top