የሠራተኞችን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ የኮንፌዴሬሽኑ ሚና ወሳኝ ነው — ክብርት ሰላማዊት ዳዊት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ኮንፌዴሬሽኑ ባለፉት ዓመታት የሠራተኞችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ሥራዎችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ክብርት ሰላማዊት ዳዊት በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኮንፌዴሬሽኑ የሠራተኞችን መብትና ተጠቃሚነትን በማስጠበቅ፣ የሠራተኛና የአሠሪ ግንኙነትን በማጠናከር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሰላምን በማስፈን ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በዘርፉ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ኮንፌዴሬሽኑን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እንደሚሠራም አመልክተዋል።
በውይይቱ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ካሳሁን ፎሎን ጨምሮ የኮንፌዴሬሽኑ አመራሮች ተሳትፈዋል።