Mols.gov.et

ከ16 በላይ የሆኑ የእህል ዘሮችን መውቃት የሚያስችለው ማሽን …

July 31, 2024
ከ16 በላይ የሆኑ የእህል ዘሮችን መውቃት የሚያስችለው ማሽን ታምራትና ጓደኞቹ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ህልም ዕውን ለማድረግ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ከተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል የተሰባሰቡት እኒህ ወጣቶች የአርሶ አደሩን ህይወት የሚያቀል የግብርና ማሽን አስራ ሁለት ሆነው አንድ ቡድን በማዋቀር በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ማሽኑ እህል መውቃት እና ጥራጥሬ መፈልፈል የሚያስችል በመሆኑ የአርሶ አደሮችን ጉልበትና ጊዜ ከመቆጠብ አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ አርሶ አደሩ ምርቱን ከማሳ ላይ ሰብስቦ ወደ ማሽኑ ማስገባት በቻ ነው የሚጠበቅበት ፡፡ ገላባ በማንሳት ፣እብቅ በማራገብ አይደክምም፡፡ በሌላ በኩል ወንፊት የተገጠመለት በመሆኑ ገለባና አላስፈላጊ ነገሮችን መለየት ይችላል፡፡ ይህም የእናቶች ድካም ለመቀነስ ያስችላል፡፡ ‹‹የእኛ ማሽን ከውጭ ከሚገባው እና አሁን ገበያ ላይ ካለው በዋጋ፣ በጥራት እና በአገልግሎት አሰጣጡም በጣም የተሻለ ነው›› የሚሉት ወጣቶቹ ከውጭ የሚገቡት ማሽኖች በአብዛኛው እንድ ዓይነት እህል ብቻ የሚወቁ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ጤፍ የሚወቃ ከሆነ ማሽላ ላይወቃ ይችላል ፤ በቆሎ ወይም ሩዝ የሚፈለፈል ከሆነ ሌላ ነገር ላያደርግ ይችላል ፡፡ እነ ታምራት ያመረቱት ማሽን ግን 16 ዓይነትና ከዚያ በላይ የሆኑ እህሎችን መውቃት እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ ሌላው ማሽኑን ልዩ የሚያደርገው ተበታትኖ የሚታሰርና የሚፈታታ እንደገናም በቀላሉ መገጣጠም የሚቻል መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁኔታውም ማሽኑን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ምቹ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች አካባቢያዊ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማሽኑ በጄኔሬተር ፣ በጸሐይ (በሶላር) እና በኤሌክትሪክ ኃይልን በመጠቀም መስራት የሚችል መሆኑ ደግሞ ችግር ፈቺነቱን የላቀ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ታምራትና ጓደኞቹ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተመቻቸው የሠመር ካምፕ ፕሮግራም ተሳታፊ በመሆናቸው የፈጠራ ሥራቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደቻሉ ይገልፃሉ፡፡ የሠመር ካምፕ ቆታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የራሳቸውን ካምፓኒ የማቋቋም ዕቅድ ይዘዋል፡፡ በቀጣይም ያመረቱትን ማሽን ወደ ተጠቃሚው ደርሶ የአርሶ አደሩ ችግር ሲፈታ ለማየት በእጅጉ ጓጉተዋል፡፡ በእህል አሰባሰብ ወቅት የሚከሰተው የምርት ብክነት ተወግዶ አርሶ አደሩ በድካሙ ልክ ተጠቃሚ የሚሆንበትንና የዜጎች የምግብ ዋስትና የሚረጋገጥበትን ጊዜም በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡
tigTIG
Scroll to Top