ISO 9001- 2015 የአገልግሎት ጥራት ስታንዳርድ
October 27, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለመላ ሠራተኞች እየሰጠ በሚገኘው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መድረክ ላይ በISO 9001- 2015 የአገልግሎት ጥራት ስታንዳርድ ለይ ያተኮረ ገለፃ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል፡፡
በሥልጠናው መጀመሪያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ነቢሃ መሃመድ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ አገልግሎትን በጥራት ለመስጠት የሚያስችል ስታንዳርድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች ወጥና ቋሚ በሆነ መልኩ ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ከማስቻል አንፃር የISO 9001- 2015 የአገልግሎት ጥራት ስታንዳርድ የበለጠ ተመራጭ ሆኖ መገኘቱን የገለፁት ክብርት ወ/ሮ ነቢሃ አሠራሩን በሚኒስቴር መ/ቤቱና አስር የፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ቁጥራቸው 40 ለሚሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራርና ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡
ሥልጠናውን የወሰዱት ባለሙያዎች በሚኒስቴር መ/ቤቱ ውስጥ የሚገኙ እያንዳንዱን የሥራ ክፍል የአሰራር ሥርዓትን መሰረት ያደረጉ ከ200 በላይ የጥራት ስታንዳርድ ሰነዶች ማዘጋጀታቸውንና በቀጣይም ኢኒስቲትዩቱ በሚሰጠው አስተያየት መሰረት ተሻሽለው ወደ ሥራ እንደሚገቡም ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የISO 9001- 2015 የአገልግሎት ጥራት ስታንዳርድ መተግበሩ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እና የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያችል ከመሆኑም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በላይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋም እንደሚያደርገውም በመድረኩ ተገልጿል፡፡