የብሩህ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ውድድር የሽልማት አሸናፊዎች የንግድ ልማት ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
June 26, 2023
እየተካሄደ በሚገኘው አራተኛው ብሩህ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ውድድር የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ስለ ውድድሩ አካሄድ ማብራሪያ የሰጡት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው።
በንግግራቸውም ማሰልጠን፣ መሸለም፣ ማብቃት በሚል መርህ የሚከናወነው ውድድር በ2013 ዓ.ም ተጀምሮ ሰባት ውድድሮች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ከዚህ ቀደም በተካሄዱ 7 ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ውድድሮች በአጠቃላይ 2,412 አመልካቾች የተሳተፉ ሲሆን ለ400 ሃሳብ ባለቤቶች ወይም 552 ወጣቶች የቡትካምፕ ስልጠና ተሰጥቷል።
በአጠቃላይ ለ 167 ምርጥ ሃሳቦች የ 1,518,000 ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል ብለዋል።
ብሩህ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሀሳቦች ውድድር ፕሮግራም በኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ እና በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን ለማበረታታት የተዘጋጀ የውድድር መርሐ ግብር መሆኑንም ገለፀዋል።
እስካሁን በነበሩት ውድድሮች ለአሸናፊዎች የንግድ ማብቃት ተግባር መከናወኑን የተናገሩት ክቡር አቶ ንጉሡ ለዚህ ዓመት ብሔራዊ ውድድር 50 ተሸላሚዎች ለቀጣዮቹ 3 ወራት የንግድ ሥራ ልማት ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ብሩህ ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር 1,137 የክልል እና የዩኒቨርሲቲ አመልካቾችን በማሳተፍ የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸውን ሲያወዳድር ቆይቷል።