352ኛው የዓለም የሥራ ድርጅት የበላይ አካል (Governing Body) ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ትልቅ መድረክ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ የተመራ የልዑካን ቡድን በመሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡
በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው እና ሌሎች የቴክኒክ ባለሙያዎችም ሃገራችን በመወከል በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡
ከክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና አሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ አኳያ ተቀርፀው ተግባራዊ በተደረጉ የሪፎርም ሀሳቦች ማህበራዊ ፍትህን በማንገስ ዘላቂ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የዓለም የሥራ ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ተቀራርባ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ባሳለፈው ዓመት በጄኔቭ በተካሄደው 112ኛው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ኮንፈረንስ ላይ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሥራ ድረጅት ምክትል የበላይ አካል (ILO governing body) ሆና መመረጧ ይታወሳል፡፡