Mols.gov.et

ከአርባ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

July 27, 2024
ከአርባ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ጋር ተፈራርሟል፡ ስምምነቱ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ በሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ/Agricultural sample survey/ ላይ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሰራተኞች ለምቶ ወደ ሥራ የገባውን የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን በመጠቀም ለመቅጠር የሚያስችል ነው፡፡ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፣ የሥታስቲክስ አገልግሎቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ባለፉት ዓመታት በገጠርና በከተማ ግብርና እንዲሁም በሌማት ትሩፋት የተሠሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት በትክክል ለመለካት የሚያስችል በመሆኑ ለሀገር በቀል ሪፎርም ሥራችን ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ከ22 ዓመታት በሁዋላ በሚሰበሰበው በዚህ ሥራ መረጃውን የሚያሰባስቡ ዜጎች ምልመላና ቅጥር በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሠራተኞች ለምቶ ወደ ሥራ በገባው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (ELMIS) አማካኝነት እንዲፈፀም ለማስቻል ስምምነቱ መደረጉን የገለፁት ክብርት ሚኒስትር ይህም ፍትሃዊ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የቅጥር ሂደቱን በማጠናቀቅ በፍጥነት ሥራውን ለማስጀመር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች የለማው የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት የሥራ ገበያውን ማዘመን ፣ ገበያው የሚፈልገውን የክህሎት አይነት መለየትና በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለዜጎች በፍትሃዊነት የመፍጠር ዓላማ ያለው መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ሥርዓቱን ለመጠቀም ያሳየው ተነሳሽነት ለሌሎችም ተቋማት አርአያ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር በከር ሻሌ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በመላ ሀገሪቱ የሚተገበርና መረጃዎችን በአጭር ጊዜና በጥራት ለማሰባሰብ የሚያስችል መሆኑ የሥታስቲክስ አገልግሎቱ ለሚያካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ በላቀ ደረጃ ተመራጭ እንዳደረገው ገልፀዋል፡፡ በመረጃ ማሰባሰብ ሥራው ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በየአካባቢያቸው በሚገኙ የሥራ ዕድል ፅ/ቤት በመገኘት የባዮሜትሪክ መረጃቸውን በመስጠት መመዝገብና በሥራው ላይ መሰማራት እንደሚችሉም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
oroORO
Scroll to Top