ወጣቶች ለሀገር ልማት እና ብልጽግና ጉልህ አስተዋጽዎ እያበረከተ ወደ ሚገኘው የብየዳ ሥራ መምጣት ይጠበቅባቸዋል ተባለ፡፡
ሚያዝያ 15, 2025

ወጣቶች ለሀገር ልማት እና ብልጽግና ጉልህ አስተዋጽዎ እያበረከተ ወደ ሚገኘው የብየዳ ሥራ መምጣት ይጠበቅባቸዋል ተባለ፡፡
3ኛው የአፍሪካ ብየዳ ፌዴሬሽን መደበኛ ዓመታዊ ጉባዔ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመሯል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት በጋራ ባዘጋጁት በዚህ ጉባኤ በብየዳ ዘርፍ የአፍሪካ ተወዳዳሪነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር፣ የልምድ ልውውጥ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የብየዳ ክህሎት ውድድር እና የመስክ ጉብኝት ይደረጋል ተብሏል፡፡
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ይተፋ ፤ መድረኩ የአፍሪካ ወጣቶች በክህሎት ለማስተሳሰር እና ተወዳዳሪ አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ተሻለ በሬቻ በመልዕክታቸው የብየዳ ሳይንስ በአሁን ወቅት እጅግ እየረቀቀ ከመምቱን ባሻገር ከትናንሽ ሥራዎች እስከ ሜጋ ፕሮጀክቶች የብየዳ ክህሎት እንደሚፈልጉ ገልጸው ወጣቶች ለሀገር ልማት እና ብልጽግና ጉልህ አስተዋጽዎ እያበረከተ ወደ ሚገኘው እና ከፍተኛ ተከፋይ ወደ ሚያደርገው የብየዳ ሥራ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር በበኩላቸው ኢትዮጵያ አለም አቀፍ እዉቅና ያለው የብየዳ ማዕከል ባለቤት መሆኗን ጠቁመው መሰል መድረኮች አለምአቀፍ ልምድ ስለሚገኝባቸው እንደ ትልቅ የልምድ ልውውጥ መድረክ ሆነው ያገለግላሉ፡፡
መድረኩ ለቀጣይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆኑ 16 የሚደርሱ የአፍሪካ ሀገራት እና ልምዳቸውን የሚያጋሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይሳተፋሉ፡፡







