የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በፍፁም ስነ ምግባር፣ ለዜጎች በመጠንቀቅ፣ በኃላፊነትና ሀገርን በመውደድ ስሜት ሊተገበር ይገባል! ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
April 13, 2025

የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በፍፁም ስነ ምግባር፣ ለዜጎች በመጠንቀቅ፣ በኃላፊነትና ሀገርን በመውደድ ስሜት ሊተገበር ይገባል!
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እየተገበራቸው በሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች ለውጥ ካስመዘገበባቸው መስኮች መካከል የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ቀዳሚው ነው፡፡
አሠራሩን ቀልጣፋና የዘመነ ለማድረግም የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (LMIS) በሚኒስቴር መ/ቤቱ ለምቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪቱ ዘመኑን የዋጁ እንዲሆን የሚያግዝ የህግ ማዕቀፎቹን የማሻሻል ሥራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ይህንኑ መነሻ በማድረግ በተቀረፀው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከውጭ ሀገር የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ስርዓትንና ህግን አክብሮ መተግበር ከተቻለ የዜጎች፣ የሀገርና የተቋማት ተወዳዳሪነት የሚረጋገጥበት ዘርፍ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥነ ምህዳሩን ምቹ በማድረግ ኤጀንሲዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ክብርት ሚኒስትር ኢንዱስትሪውን ለመቀየር የቆረጠ የኤጀንሲዎች ስብስብ በማፍራት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በላቀ ትጋት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በዘርፉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሚናቸውን በኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ህጋዊ አሰራርን በማይከተሉ ኤጀንሲዎች ሳቢያ ዜጎች ለእንግልትና ለስቃይ የሚዳርጉ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ሲፈጠሩ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡
መሰል ህገወጥ ድርጊቶችን በመከላከል የዜጎችን ክብርና ደህንነት ማዕከል ያደረገ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ሥርዓት እውን ለማድረግም የአዋጅ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ህጋዊ አሠራርን ተከትለው ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡ ኤጀንሲዎችን እውቅና ለመስጠት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ኤጀንሲዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ የሚያግዝ ወጥ የሆነ አደረጃጀት በቀጣይ ለመፍጠር በእቅድ መያዙንም ክብርት ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡
በተለያየ ጊዜ የሚደረጉት የህግም ሆነ የአዋጅ ማሻሻያዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት በአስተሳሰብና በባህሪ ለውጥ ሲታጀቡ መሆኑን የገለፁት ክብርት ሚኒስትሯ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት በፍፁም ስነ ምግባር፣ ለዜጎች በመጠንቀቅ፣ በኃላፊነትና ሀገርን በመውደድ ስሜት ሊተገበር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡





