የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ የመፃኢ ጊዜ እድላችንን ከሚወስኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
August 28, 2024
የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ የመፃኢ ጊዜ እድላችንን ከሚወስኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
“ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት” በሚል መሪ ሃሳብ ከመላው ሀገሪቱ ለተወጣጡ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች ስልጠና መሰጠት ጀመረ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ አሁን ያለንበት ጊዜ እውቀት ብቻውን ምሉዕ እንደማያደርግ ከግምት በማስገባት ዓለም ላይ ለክህሎት ልማት ልዩ ትኩረት የተሰጠበት ወቅት ነው፡፡
እኛም እንደ ሀገር በዘርፉ መሰረት ለመጣል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ለሀገራዊ ፍላጎቶቻችን ምላሽ የሚሰጥ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ይህም በቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ላይ ይስተዋል ነበረውን ክፍተት የሚሞላ ብቻ ሳይሆን የሥልጠና ስርዓታችን ጊዜውን የዋጀና ለሀገራዊ ልማትና ብልጽግና ጉዞ የበኩሉን ድርሻ መወጣት የሚችሉ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያስችላል፡፡
ፖሊሲውን ተከትሎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተግባራዊ ያደረገው አዲሱ የዘርፉ እሳቤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ ልማት ፍላጎት የሚመልስ፣ በዘርፉ የነበሩ አለመጣጣሞችን የሚፈታ እንዲሁም አሰልጣኞችም ሆኑ ሠልጣኞች ምርታማ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ይህም የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ እንደ ሀገር የመፃኢ ጊዜ እድላችንን ከሚወስኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አሁን የሚሰጠው ስልጠና በዘርፉ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና አዳዲስ እሳቤዎች ላይ አሰልጣኞች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ ባህሪያዊና ቴክኒካዊ ብቃቶችን በማሳደግ ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 12 ቀናት በ17 የስልጠና ማዕከላት የሚሰጠው ስልጠና በዘርፉ ልህቀትን ለማምጣት የሚያስችል እንደሆነ ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር በመድረኩ 24 ሺህ የሚጠጉ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡