የተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከመቀየር ባሻገር የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አንፃርም ጉልህ ድርሻ አለው፤ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
March 19, 2025

የተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከመቀየር ባሻገር የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አንፃርም ጉልህ ድርሻ አለው፤
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከእናት ባንክ ፣ ከኢንተርፕርነሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) እና ከተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ (UN women) ጋራ በመተባባር ‹‹ብሩህ-እናት›› በሚል ስያሜ ያዘጋጀው የሴቶች የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ተጀመረ፡፡
በውድድሩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች የሚደግፉ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ተግባራዊ ማድረግ በዘርፉ የሪፎርም ሥራዎች ቅድሚያ ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ ቀዳሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከእነዚህ ፕሮግራሞች መካከል ‹‹ማሰልጠን፣ መሸለም፣ እና ማብቃት›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ‹‹ብሩህ ኢትዮጵያ›› ሀገር አቀፍ የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በብሩህ ኢትዮጵያ ጥላ ሥር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በፍትሃዊነት የሚያሳትፉ የፈጠራ ሃሳብ ውድድሮች በየአመቱ እየተካሄዱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የብሩህ ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ወንድና ሴት ወጣቶችን በጋራ የሚያሳተፍ ቢሆንም በፈጠራና ኢኖቬሽን ዘርፍ ሴቶች ጉልህ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል የ‹‹ብሩህ እናት›› የሴቶች የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር መዘጋጀቱን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
የሴቶችን የሥራ ጫና በማቃለል በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ የፈጠራ ውጤቶችን ማበረታታትና ማሳደግ የውድድሩ ዋንኛ ዓላማ መሆኑንም ተጠቁሟል፡፡
የተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከመቀየር ባሻገር የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አንፃር ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተወዳዳሪዎች የቡት ካምፕ ቆይታቸውን ሃሳባቸውን ይበልጥ ለማበልፀግና ለማላቅ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡
ውድድሩ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የተመዘገቡ 612 የፈጠራ ሀሳቦች በተመረጡ ዳኞች ተወዳድረው ወደ ቡት ካምፕ የሚገቡ 50 የፈጠራ ሀሳቦች መለየታቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ተወዳዳሪዎች ከመጋቢት 9/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ቀናት በቡት ካምፕ በሚኖራቸው ቆይታ የኢንተርፕረነርሺፕ ስልጠና ይሰጣቸዋል፤ የምክር ድጋፍም ያገኛሉ፡፡
በየደረጃው በሚካሄዱ ውድድሮች የሚለዩ 10 አሸናፊዎችም ከብር ከ100 ሺህ እስከ 500ሺህ ድረስ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡









