Mols.gov.et

የማኅበረሰብ አቀፍ ምክክርን ለአካባቢያዊ ጸጋ ልየታና ለምርታማነት

February 1, 2025
የማኅበረሰብ አቀፍ ምክክርን ለአካባቢያዊ ጸጋ ልየታና ለምርታማነት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እየተገበራቸው ከሚገኙ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች መካከል በሥራ ባህል ላይ ለውጥ የሚያመጡና ምርታማነትን የሚያጎለብቱ የማኅበረሰብ ምክክሮችን በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ማካሄድ አንዱ ነው፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በ2016 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ ምክክር ለማካሄድ የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርፆና ለውይይት አመቻቾች ተገቢውን ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በዚሁ መሰረት በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በአስር ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በተካሄዱ ምክክሮች ከ2ሚሊዮን የሚልቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የማኅበረሰብ አቀፍ ምክክር አፈፃፀም ከክልል አስተባባሪዎች ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡ በተለያየ ደረጃ በተካሄዱት ምክክሮች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ያሉ አካባቢያዊ ፀጋዎች እየተለዩ ሲሆን እንደየአካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ኅብረተሰቡን ምርታማ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ዕድሎችና ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጭምር ነዋሪዎች ውይይት እንደሚያደርጉ በመድረኩ ተብራርቷል፡፡ ተወያዮች ከሥራ ባህል ጋር ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሔን ከማመላከት ባሻገር አከባቢያዊ አቅሞችን በመጠቀምና የራሳቸውን ድርሻ በመውሰድ ወደምርት የሚያስገቡ ፕሮጀክቶችን ወደመቅረጽ እየተሸጋገሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በቀጣይም የሥራ ባህል ግንባታና የምርታማነት የማኅበረሰብ ምክክር በተካሄዱባቸው አካባቢዎች “በአንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት” በሚል መሪ ሃሳብ ከምክክር የሚመነጩ የፕሮጀክት ሀሳቦችን በማኅበረሰብ ባለቤትነት ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችሉ የፀጋ ልየታው ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል፡፡
en_USEN
Scroll to Top