ዜጎች ዕውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ወደ ኮሌጆች መምጣት እንዳለባቸው ተገለፀ።
March 23, 2025

ዜጎች ዕውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ወደ ኮሌጆች መምጣት እንዳለባቸው ተገለፀ።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የፖለቲካ እና የድርጅት ሥራዎች የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ባለፉት ስምንት ወራት የተሠሩ ሥራዎችን እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ውይይቱ አቅርቧል፡፡
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) በበጀት ዓመቱ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን አንስተዋል፡፡
ለዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙንም ነው ያስታወሱት፡፡
እስካሁን ድረስም ለ657 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ ይህም የዕቅዱን 53 በመቶ ነው ብለዋል፡፡
የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል 70 በመቶ የሚኾኑት ቋሚ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለ50 ሺህ ዜጎች ደግሞ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት መሰጠቱን ነው የተናገሩት፡፡
መሪዎች ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥተው በቁርጠኝነት መሥራታቸውንም አመላክተዋል፡፡ በሥራ ዕድል እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክር ቤት አማካኝነት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው በየወሩ እየተገመገመ መመራቱንም አንስተዋል፡፡
ውጤታማ ሥራ የሠሩ ከተሞች እና ዞኖች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ የመረጃን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ ቀልጣፋ እና ቀላል ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ 246 ኮሌጆች አሉ ያሉት ኀላፊው 210 የሚኾኑት ኮሌጆች ዲጅታላይዝድ በኾነ መንገድ እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሁሉም ነገር በሲስተም ይሠራል፤ ቀሪዎቹም ወደ ሲስተም ይገባሉ ነው ያሉት፡፡
የሥራ ዕድልም ኾነ የኮሌጆች የሥልጠና ሂደት በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ዲጅታላይዝድ ነው ብለዋል፡፡ ሥራን ዲጅታላይዝድ ማድረግ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማስቀረት እንዳስቻለም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሃሰተኛ ሪፖርቶች እንደማይኖሩም አስረድተዋል፡፡
በየዞኑ እና በየወረዳው ለሸድ መገንቢያ የሚውል የቦታ አቅርቦት ችግር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ የሸድ መገንቢያ ቦታ አቅርቦት ብቻ ሳይኾን የገንዘብ እጥረትም እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ኮንቴነሮች እና ሸዶች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙትን የማስመለስ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ነው የገለጹት፡፡ ያልተመለሱ ሸዶችን እና ኮንቴነሮችን መመለስ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ለዞኖች መሰራጨቱንም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በጸጥታ ችግር ምክንያት ሁሉም ዞኖች ሥራውን በውጤታማነት እየተጠቀሙበት አይደለም ነው ያሉት፡፡ በጀቱን በፍጥነት መጠቀም እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባልም ብለዋል፡፡
በ246 ኮሌጆች 198 ሺህ ተማሪዎች ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር የተናገሩት ኀላፊው እስካሁን ድረስ 72 ሺህ ተማሪዎች ብቻ ወደ ኮሌጆች ገብተዋል ነው ያሉት፡፡
በጸጥታ ችግር ምክንያት ተማሪዎች በሚጠበቀው ልክ ወደ ኮሌጆች እየገቡ አይደለም፣ ኮሌጆችም በተገቢው መንገድ እየሠሩ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በትውልድ ላይ ክፍተት ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
“ዜጎች ዕውቀት እና ክህሎት ኖሯቸው የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ወደ ኮሌጆች መምጣት አለባቸው” ያሉት ኀላፊው ዕውቀት እና ክህሎት ሳይኖራቸው የሥራ ዕድል አንፈጥርም ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ አራት ወራት ሥራዎችን በስኬታማነት ለመሥራት አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል፡፡
የጸጥታ ችግሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተማሪዎችን በኮሌጆች ለመቀበል እንቅፋት መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡
የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና የተመረቱ ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብም የጸጥታ ችግሩ እንቅፋት እንደኾነ ነው ያነሱት፡፡ የብድር ሥርጭቱ በአግባቡ እንዳይሰራጭ እና እንዳይመለስ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራን ከተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የውጭ ሀገር ስምሪቱም በሕጋዊ መንገድ እየተፈጸመ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶች ባሉበት አካባቢ ኾነው በመመዝገብ እና በኮሌጆች በመሠልጠን ወደ ውጭ መሄድ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ስለኾነ ተጠቃሚ መኾን መቻል አለባቸውም ነው ያሉት፡፡ ዘገባው የአሚኮ ነው።




