የሀገር ህልውና እና እድገት የሚረጋገጠው ሥራ በሚፈጥሩ ግለሰቦች ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
September 7, 2024
የሀገር ህልውና እና እድገት የሚረጋገጠው ሥራ በሚፈጥሩ ግለሰቦች ነው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
“ፈጠራን በክህሎት” በሚል መሪ ሀሳብ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ የመጀመሪያ በሆነው የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ባለፈው አንድ ዓመት በተሳታፊ ወጣቶች የተሠሩ ቴክኖሎጂዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የቴክኖሎጂ ኤክስፖውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ የተደረጉ ቴክኖሎጂዎች እንደ ሀገር ብልጽግና ለማረጋገጥ ከተቀመጡ ፒላሮች በእጅጉ የተሳሰሩ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቴክኖሎጂ እና ቱሪዝም ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀገር ህልውና እና እድገት የሚረጋገጠው ሥራ በሚፈጥሩ ግለሰቦች መሆኑን የጠቆሙት ክቡር ጠየቅላይ ሚኒስትር ፕሮግራሙ ወጣቶች እጃቸውን፣ አዕምሮአቸውን እና ልባቸውን አገናኝተው ከሰሩ አስደማሚ ነገር መስራት እንደሚችሉ ያየንበት ነው ብለዋል፡፡።
ቴክኖሎጂዎቹ ኢትዮጵያ ፋብሪካ መፍጠር የምትችል ሀገር መሆኗን ያረጋገጡ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቀጣይ የማባዛትና ማስቀጠል ሥራ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል። መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ፕሮግራሙ በዘርፉ የመጀመሪያና ፋና ወጊ ነው ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ላለፉት 12 ወራት በተለያ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሀሳብ ውድድሮች አሸናፊ የነበሩ 400 ገደማ ወጣቶችን ከመላ ሀገሪቱ ክፍል ያሰባሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ተሳታፊዎች በቆይታቸው ቴክኖሎጂያቸውንና የፈጠራ ሀሳባቸውን ሊያሳድግ የሚችል የንድፈ ሀሳብና የተግባር ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉንና በ12 ወር ቆይታቸው በ11 ዘርፎች ችግር ፈቺና ሀብት አመንጪ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን መስራት እንደተቻለም ነው ክብርት ሚኒስትር የገለጹት፡፡
ከዚህ ውስጥ 45 የሚሆኑት የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ጥበቃ ምዝገባ ሰርተፊኬት ያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹም ሂደቱን እየጨረሱ ይይገኛሉ ብለዋል፡፡
የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የተናጠል ጉዟቸውን አቁመውና ኩባንያ የመሆን ርዕይ ሰንቀው በ78 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የተወሰኑት ምርቶቻቸውን እስከ ውጭ ሀገር እስከ መላክ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ሥራ ኢትዮጵያ የጀመረችው ራስን የመቻል ጉዞ እንዲሳካ ተኪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት እንድናመርት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሰጡን አመራር ተግባራዊ የተደረገ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትር በርካታ ባለድርሻና አጋር አካላትም የተሳተፉበት ነው ብለዋል፡፡
ኤክስፖው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና የኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጁት ሲሆን እስከ ጳጉሜ 4 ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡