ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር …
April 22, 2025

ክልል አቀፍ የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና ተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች እንደሚካሄድ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት መሰጠ ቱም ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ክልል አቀፍ ውድድሩን በማስመልከት በሶዶ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ በዛብህ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ በክልሉ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በተለይ በመካከለኛ ደረጃ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ይህም የኢ-ፍትሃዊነት ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል።
በሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች የሚካሄደው የቴክኖሎጂ፣የክህሎት እና የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድር ዓላማ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ኢንተርፕራይዝ ለማሽጋገር ታስቦ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቴክኖሎጂም የማህበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ ተቋማት ቴክኖሎጂዎችን በመቅዳትና በማባዛት ሀብት እንዲያመነጩ ታስቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ውድድርም ጥናታዊ ሥራዎች በመደርደሪያ የሚቀመጡ ሳይሆን ቴክኖሎጂ፣ ምርት እና አገልግሎት ሆነው እንዲወጡ ነው ብለዋል።
ለአራት ቀናት በሚቆየው ክልል አቀፍ ውድድር በክህሎት ዘርፍ በ20 ሙያዎች፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ በ14 ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም በስድስት የተግባራዊ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ውድድር ይካሄዳል ብለዋል።
በውድድሩም የተለያዩ አሠልጣኝ መምህራን፣ ሠልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች እንደሚሳተፉም ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።

