Mols.gov.et

ከረዳትነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት…

February 1, 2025
ከረዳትነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት… ወጣት አምሀ በቀለ ይባላል፡፡ ነዋሪነቱ በሐረር ከተማ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በአንድ ግለሰብ የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት ውስጥ በረዳትነት በመቀጠር ነበር የሥራውን ዓለም የተቀላቀለው፡፡ ሥራ ከጀመረባት የመጀመሪያዋ ዕለት አንስቶ እያንዳንንዱ ነገር እንዴት እንደሚሰራ በትኩረት ያስተውል እንደነበር ይናገራል፡፡ ከዕለት ወደ እለትም ለሙያው ያለው ፍቅር እየጎለበተ ሄዶ በስድት ወር ቆይታ ብቻ ራሱን ችሎ የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን መስራት የሚችል ባለሙያ ለመሆን በቃ፡፡ ችሎታውንና ብቃቱን ያስተዋሉት ቀጣሪዎቹ የሚሰጡት ማበረታቻ የበለጠ ጉልበት ሲሆነው ፈጠራን ጭምር በማከል በሚሰራቸው ቁሳቆሶች የረኩ ደንበኞችም አድናቆትን ያጎርፉለት ጀመር፡፡ ‹‹ለአምስት ዓመታት በቅጥር በቆየሁበት ጊዜ የቀሰምኩት ልምድ ክህሎቴንና እንዳዳብርና የደንበኞችን ፍላጎት እንድረዳ ዕድል የሰጠኝ ከመሆኑም በላይ የራሴን ሥራ ለመጀመር የሚያስችል በራስ መተማመን አላብሶኛል ›› ይላል አምሀ፡፡ በዚህ መሰረት ቆጥቦ ባጠራቀመው ገንዘብ ላይ ከቤተሰብ ያገኘውን የፋይናንስና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ አክሎበት የራሱን ሥራ አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ ምንም እንኳን ለአዲስ ቢዝነስ ጀማሪ በገበያው ላይ ተቀባይነትን ማግኘት ቀዳሚው ፈተና ቢሆንም አምሀ ግን ጥራት ያለውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋና በፍጥነት በማቅረብ የገበያ ማጣትን ተግዳሮት መሻገር እንደቻለ ይገልፃል፡፡ ሥራውን በየዕለቱ ማሳደግና በገበያ ላይ ያለው ተቀባይነት የላቀ እንዲሆን ማስቻል ዋንኛ ግቡ በመሆኑ የሚያገኘውን አብዛኛውን ትርፍ ቢዝነሱን ለማስፋፋት እንደሚያውለው ይናገራል፡፡ ኪችን ካቢኔት፣ ቁምሳጥን፣ ኮንትሮል ቡፌና የውስጥ በሮች አምሀ በጥራት የሚሰራቸውና ተለይቶ የሚታወቅባቸው ምርቶች ናቸው፡፡ ‹‹የትኛውን የእንጨት ውጤት በልዩነት መስራት እንደምችል ማወቄ ምርቶቼ የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖራቸው አድርጓል›› የሚለው ወጣት አምሀ በአካባቢው ምን አይነት ምርት በስፋት ይፈለጋል የሚለውን ለመገንዘብም ገበያውን በየጊዜው እንደሚያጠናም ይናገራል፡፡ ዘመናዊ የማምረቻ መሳሪያዎችን መጠቀም የምርትን ጥራት ለማረጋገጥ የሚስችል እንደመሆኑ አዳዲስ ማሽነሪዎችን ለማሟላት በየጊዜው ጥረት ከማድረግ ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ ከዚህም አልፎ ግን የፈጠራ ብቃቱን በመጠቀም ሥራን ሊያቀሉ የሚችሉ መሳሪያዎችን ራሱ ሰርቶ በመጠቀም ላይ ይገኛል፡፡ ከ2010 ጀምሮ በግል ኢንተርፕራይዝነት መመዝገቡ ደግሞ የሥራውን ውጤታማነቱ የሚያረጋግጡ መንግስታዊ ድጋፎችን ለማግኘት በር ከፍቶለታል፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የምርቱን ጥራት የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ሙያዊ ብቃቱን በምዘና ማረጋገጡና የፈጠራ ሥራዎቹ ሀገር አቀፍ እውቅናን ማግኘት መቻላቸውንም ይናገራል፡፡ አምሃ በአስር ሺ ብር የጀመረው ቢዝነስ ዛሬ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላይ ደርሷል፤ ለሰባት ወጣቶችም ቋሚ የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፡፡ ከውጭ የሚገቡ መምርቶችን በአይነትና በጥራት የሚወዳደር፣ በገበያ ላይ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ምርት የማምረት ብሎም ኢትዮጵያዊ ምርቶችን ለዓለም ገበያ የማቅረብ ህልምን የሰነቀው አምሀ በሀረሪ ክልል በተገነባውና ለእንደእርሱ አይነት ውጤታማ ወጣቶች በተመቻቸው ምቹና ደረጃውን የጠበቀ የማምረቻ ማዕከል ውስጥ ቀን ከሌት በትጋት ይሠራል፣ አእምሮውን ፣ ልቡንና እጆቹን በማቀናጀት ውብና ድንቅ የሙያ ውጤቱን ለደንበኞቹ እያቀረበም ይገኛል፡፡
en_USEN
Scroll to Top