Mols.gov.et

አነስተኛ ወጪ፣ ትልቅ ተጽዕኖ፤ ለሚሊዮኖች ተስፋ የሆነው የሰመር ካምፕ ውጤት…

July 5, 2024
አነስተኛ ወጪ፣ ትልቅ ተጽዕኖ፤ ለሚሊዮኖች ተስፋ የሆነው የሰመር ካምፕ ውጤት… በአሁን ወቅት ቤት መስራት ለበርካቶች እጅግ ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ የቤት ግንባታን ፈታኝ ካደረጉት ጉዳዮች መካከልም ከመሬት ዋጋ ባሻገር የመሥሪያ ግብዓት ዋጋ መናር ተጠቃሽ ምክንያት ነው። ቤት ከሚሰራባቸው ግብዓቶች መካከል ደግሞ አንዱ ብሎኬት ነው፡፡ የብሎኬት ዋጋ በቤት አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣም በዘርፉ ባለሙያዎች ይነገራል፡፡ ለብሎኬት ዋጋ እና ምርት ደግሞ የሲሚንቶ አቅርቦት እና ዋጋ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ የብሎኬትን ዋጋ ለማረጋጋት ሲሚንቶን የሚተካ አማራጭ ማሰብ ሌላኛው መፍትሄ ነው፡፡ ይህንን የተገነዘቡት ግርማ እና ጓደኞቹ ለዚህ ችግር መፍትሄ ያሉትን ቴክኖሎጂና በቴክኖሎጂውም የሚሰራውን ተሰካኪ(interlocking) ብሎኬት ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ማሽኑን ለመስራት የተነሳሱት ከዚህ ቀደም ለዚህ አገልግሎት ከቻይና የሚገባው ማሽን በመጠኑ ትልቅ፣ በዋጋው ውድ እንዲሁም ጥገናውም አዳጋች በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአንጻሩ አሁን የሰሩት ማሽን የትም ቦታ ተነቃቅሎ በቀላሉ ማንቀሳቀስ የሚቻልና በቀላል ወጪ የሚጠገን እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ መቅረብ የሚችል ማሽን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ማሽን ተጠቅመው የሚያመርቱት ብሎኬትም የአገልግሎት እድሜው ከመደበኛው ብሎኬት እጅግ ረዥም ዓመት የሚያገለገል መሆኑ መረጋገጡንም ያስረዳሉ፡፡ በዚህም በተለይ የገጠር ቤቶችን ለመቀየር እና ቤት የመስራት አቅሙ የሌላቸው ዜጎች እጅግ ባነሰ ወጪ ቤት እንዲገነቡ ያደርጋል ይላሉ፡፡ የማምረቻ ማሽኑን እና ብሎኬት በስፋት አምርቶ (mass production) ለገበያ የማቅረብ ፍላጎት ያላቸው ግርማ እና ጓደኞቹ ህልማቸውን ለማሳካት በአሁን ወቅት ሙሉ ሥራዉን አጠናቀው የሙከራ ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡ ይህ ማሽን በኤሌክትሪክ ኃይልና በማንዋል የሚሠራ ሲሆን የማምረት አቅሙንም በማኑዋል በቀን እስከ 5 መቶ ተሰካኪ ብሎኬት፤ በኤሌክትሪክ ደግሞ እስከ አንድ ሺህ ብለኬት ማምረት እንደሚያስችል ነው የተነገረው፡፡ ግርማ እና ጓደኞቹ ይዘው የመጡት ቴክኖሎጂ በሀገራችን ለሚሊዮኖች ተስፋ የሆነ ከመሆኑም ባሻገር እንደ ሀገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በእጅጉ በመቀነስ ጤናማ የኑሮ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል፣ ከደብረብርሃን እና ከወላይታ ሶዶ መጥተው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ኢንስቲቲዩት ጋር ባዘጋጁቱ የክረምት ልዩ ቆይታ(summer camp) የተገናኙት እነዚህ ወጣቶች ባላቸው የተቀራረበ ክህሎት እና ማሳካት በሚፈልጉት ያጋራ ህልም በአንድ ተደራጅተው ወደ ትልቅ ኢንተርፕራይዝ ለመሸጋገር እየተጉ ይገኛሉ፡፡
en_USEN
Scroll to Top