በአዲስ አበባ በተቀናጀ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ሰፊና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሠራ ተጠቆመ
ፕሮጀክቱን ለመጀመር የሚያስችል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ ጥራቱ በየነን ጨምሮ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ካላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ የተቀናጀ የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ እሴት ሰንሰለትን መሰረት በማድግ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ቀደም ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስ በአዳማና በሀዋሳ ከተማ ወደ ሥራ በማስገባት ለበርካታ ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡
ከዚህ ሥራ የተገኙ ልምዶችን በማላቅ የአዲስ አበባ ወጣቶችን በማደራጀት ከመኖ አቅርቦት ጀምሮ በሥራው ላይ ባለው የእሴት ሰንሰለት በተቀናጀ የዶሮ እርባታ ሰፊና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የዶሮና የዶሮ ተዋጽኦ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በቅንጅት እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡