በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ተገለፀ።
March 14, 2025

በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ተገለፀ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር እያካሄደ ባለው የዘርፉ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ መስክ የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ትኩረት ያደረገ ሀገር አቀፍ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም የተጠናው ሰነድ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ውስጥ ከፍቸኛ የሆነ በሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት እንዳለ ይፋ አድርጓል።
ጥናቱን ያቀረቡት የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እንደገለፁት፤ በዋና ዋና የሀገራችን ከተሞች የተካሄደው ጥናት በመሠረታዊነት በቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ያለውን የሰው ሃይል ዝግጁነት፣ አቅርቦት እና የገበያ ፍላጎቶች ላይ ያተኮረ ነው።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በሰነዱ ላይ ጥያቄና አስተያየት አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር የመዳረሻ እና መሰረተ ልማት ማስፋፍያ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ስለሽ ግርማ ጥናቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃብት እንዲመራ ለማድረግ መሰረታዊ የአስተሳሰብ እና መዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎችን መሥራት ይገባል።
በባለሙያ ምልመላ ረገድ በኢንዱስትሪው የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እንዲፈጽሟቸው የሚጠበቁ አስገዳጅ መመሪያዎችንም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡






