Mols.gov.et

በተወዳዳሪዎች የቀረቡት ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች…

October 18, 2024
በተወዳዳሪዎች የቀረቡት ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ዲጂታል ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ መሆኑን የሚያመላክቱ መሆኑ ተጠቆመ የሴቶች ስታርታፕ ፋውንደርስ የአይሲቲ ኢኖቬሽን ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ለአስር ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚህ ውድድር 37 ሴት የፈጠራ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ አስር ተወዳዳሪዎችም እያንዳንዳቸው የአንድ መቶ ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ የሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ከሆኑት ሴቶች ተሳትፎ ውጭ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በመሆኑም ሴቶችን በልዩነት ለመደገፍና ለማብቃት የሚስችሉ አሰራሮች በስፋት እየተተገበሩ ይገኛ፡፡በዚህም በዲጂታል ዓለም ላይ ያላቸውን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማጎልበትን መነሻ በማድረግ ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው፤ ተወዳዳሪዎች በኢኮሜርስ፣ በትምህርት፣ በጤና በተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ይዘው የቀረቧቸው ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ዲጂታል ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ማሳያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫ ዲጂታላይዜሽንን የሚያበረታታ መሆኑ በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጎች መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሴቶች የዘርፉን ተለዋዋጭ፣ ኢ-ተገማችና ድንበር የለሽ ባህሪ በመረዳት ራሳቸውን ብቁ አድርገው ለመገኘት መትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ከተናጠል ይልቅ በጋራ አቅምን አስተባብሮ መስራት ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ቁልፍ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡ ውድድሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢኒስቲትዩት፣ ከኔስት ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ፣ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅትና ሌሎችም አጋር አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡
en_USEN
Scroll to Top