ስምምነቱ በተናጠል ሲሰሩ የነበሩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
March 12, 2025

ስምምነቱ በተናጠል ሲሰሩ የነበሩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሥራ ዕድል ፈጠራ ስነ-ምህዳሩ ላይ ከአዋሽ ባንክ ጋር በቅንጅት መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እና የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ፀሀይ ሽፈራው ናቸው፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሚኒስቴሩ ከክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ከመፍጠር አኳያ ግዙፍ ተልዕኮ የተሰጠው ቢሆንም ለብቻው የሚወጣው ግን አይደለም፡፡
በመሆኑም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት በርካት ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር እንደመሆኗ ለወጣቱ ጥራት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር የፋይናንስ ዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ መስራት ካልቻለ ስለዘላቂ ሰላምና ልማት ማሰብ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡
ይህንን በመገንዘብ አዋሽ ባንክ ‹‹ታታሪዎቹ›› በሚል ስያሜ በሥራ ዕድል ፈጠራ ስነ-ምህዳሩ ላይ ፋና ወጊ የሆነ ሥራ እየሰራ ያለ መሆኑን ገልፀው ለዚህም ሚኒስቴሩ ትልቅ ምስጋናና አክብሮት አለው ብለዋል፡፡
አሁን የተደረገው ስምምነትም በሁለቱ ተቋማት በተናጠል ሲሰሩ የነበሩ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ነው ክብርት ሚኒስትር የገለጹት፡፡
ክህሎት መር በሆነው የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅጣጫ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች እንደተገኙ አመላክተው በመስኩ ከዞሩ ድምሮች፣ ከአሁናዊ እና ከመጪው ጊዜ ፍላጎት አኳያ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅና የፋይናንስ ዘርፉ ሚናውን እንዲወጣም ክብርት ሚኒስትር ጠይቀዋል፡፡
የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራዉ በበኩላቸዉ፤ በሚኒስቴሩ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ከጠበቁት በላይ መሆናቸውን ገልፀው የሀገራችን የሥራ አጥነት ችግር በመንግስት ጥረት ብቻ ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡
በመሆኑም ባንካችን ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አቅርቦት እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ቆይቷል፡፡ በቀጣይም ይህን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም በሥራ ዕድል ፈጠራ መስኩ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በአዋሽ ባንክ በኩል የተፈረመው ስምምነት በሥራ ዕድል ፈጠራና የስታርት አፕ ስነ-ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ስምምነቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አቅምን መገንባት፣ የዲጂታል ኢንተርፕራይዞች እድገትን ማፋጠን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል እና የፋይናንሺያል ዕዉቀትን በማጎልበት ለክህሎት መር ሥራ ዕድል ፈጠራው ሥኬት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው፡፡



