ሰመር ካምፕ ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዕድል የፈጠረለት ወጣት
March 14, 2025

ሰመር ካምፕ ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዕድል የፈጠረለት ወጣት
እሱባለው አለልኝ ይባላል፡፡ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጀነርንግ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
የአራተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ የሠራው አንድ ፕሮጀክት በደቡብ ኢትዮጵያ በስፋት ለምግብነት የሚውለውን ዕንሰት አስመልክቶ ለማወቅና ለመረዳት ዕድል እንደሰጠው ይናገራል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከ20 እስከ 30ሚሊዮን የሚሆኑ ህዝቦች የዕንሰትን የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታቸው አካል አድርገው እንደሚመገቡ ወጣት እሱባለው ይገልፃል፡፡
ምንም እንኳን ዕንሰት እጅግ ጤናማ(gluten free) ከሚባሉ የምግብ አይነቶች መካከል የሚካተት ቢሆንም ለምግብነት የሚዘጋጅበት መንገድ ተመሳሳይና እሴት ያልተጨመረበት መሆኑ ከደቡብ ኢትዮጵያ ውጪ በሚገኙ የሀገሪቱ አካባቢዎችም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በስፋት ተደራሽ ሳይሆን እንዲቆይ አድርጎታል፡፡
ወጣት እሱባለው ያከሄደው ጥናትና ምርምር ዕንሰትን ዘመናዊ በሆነ መልኩ አዘጋጅቶና አሽጎ ለገበያ ማቅረብ ከተቻለ ምርቱ ያለውን ተቀባይነት በሥፋት ከማሳደግ ባለፈ በጓሯቸው እንሰትን የሚያበቅሉ አርሶአደሮችን ህይወት መቀየር እንደሚቻል ያመላከተ ነበር፡፡
እሱባለው ይህ የጥናት ውጤቱ መደርደሪያ ላይ ተቀምጦ እንዲቀር አልፈለገም፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም የምርምር ሥራውን ዕውን ለማድረግ የሚችልባቸውን አጋጣሚዎችንም ማማተር ጀመረ፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚዘጋጀው ‹‹ብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር›› ወደ ህልሙ የሚያደርሰው የመጀመሪያ አጋጣሚ ነበር፡፡ በውድድሩ ተሳትፎ ያገኘው የሽልማት ገንዘብና የምርምር ሥራውን ወደቢዝነስ እንዴት መቀየር እንደሚቻል የተሰጠው ሥልጠና ሥራውን በተወሰነ መጠን ለማሳደግ እንዳስቻለው ይናገራል፡፡
የ‹‹ብሩህ ኢትዮጵያ›› ተሳታፊ መሆኑና ለሽልማት መብቃቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ኢኖቬተሮችንና ቴክኖሎጂስቶችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ፈጠራቸውን ወደ ምርት እንደቀይሩ ለማስቻል ተግባራዊ ባደረገው የ‹‹ሠመር ካምፕ›› ፕሮግራም ተሳታፊ የመሆን ዕድልንም ፈጠረለት፡፡
በወረቀት ላይ ብቻ ሰፍሮ የነበረው የወጣት እሱባለው በዕንሰት ላይ የተካሄደ ጥናትና ምርምር ምቹ በሆነው የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢኒስቲትዩት ቤተሙከራ ውስጥ አድጎና ጎልብቶ በአይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ምርት ሆኖ ለመውጣት በቃ፡፡
በአሁኑ ጊዜ የእንሰት ስታርች ዱቄትን በሙከራ ደረጃ አምርቶና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አሽጎ ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኘው ወጣት እሱባለው ምርቱ ፍፁም ጤናማ መሆኑ በገበያው ላይ ሰፊ ተቀባይነትን ለማግኘት እንዳስቻለው ይገልፃል፡፡
ህብረተሰቡ በተሻለ የምግብ ይዘትና ንፅህና ስለተዘጋጀው የዕንሰት ስታርች ዱቄት ተገንዝቦ እንዲጠቀምበት ለማስቻልም የተለያዩ የኩኪስ ምርቶችን በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር የህብረተሰብ ክፍል የዕለት ምግብ ፍጆታ የሆነው እንሰት የሚሰጠውን ጠቀሜታ በማላቅ የህበረተሰቡን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ዋንኛ ግቡ እንደሆነ ይናገራል፡፡
የእንሰት ምርት ውጤቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት ከማቅረብ ባለለፈ ምርቱን በሙከራ ደረጃ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ ያደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ምላሽ አግኝቷል፡፡
ወጣት እሱባለው የጥናትና ምርምር ውጤቱ ወደ ምርት ተቀይሮ ለገበያ መብቃቱ ታላቅ የስኬት መንፈስን አላብሶታል፡፡
የምርት መጠኑ እያደገና የገበያ ተደራሽነቱም እየሰፋ መሄድ ከቻለ ዕንሰትን እያለሙ ከዕለት የምግብ ፍጆታቸው ባለፈ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ያለገኙ አርሶ አደሮችን ህይወት ተቀይሮ የሚያይበትን ቀን ሩቅ እንደማይሆን በፍፁም እርግጠኝነት ይናገራል፡፡
