ለፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች፣ ለኢንተርፕራይዞችና ለህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚዎች የሚደረገውን ድጋፍ…
August 13, 2025
ለፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች፣ ለኢንተርፕራይዞችና ለህጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚዎች የሚደረገውን ድጋፍ በፋይናንስ አቅርቦት ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ስምምነት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ የሚያመነጩ ኤኖቬተሮችንና ስታርታፕ ቢዝነሶችን መደገፍና ለውጤታማነት ማብቃት አንዱ ነው፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዚህ መልኩ ለፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶችና ለኢንተርፕራይዞች የሚያደርገውን ድጋፍ በፋይናንስ አቅርቦት ለማጠናከር የሚያስችል ሥምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አካሂዷል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ባለፉት ሁለት ዓመታት‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› በሚል ፕሮግራም በመቶዎች የሚቆጠሩ ቴክኖሎጂዎችን አበልፅጎ ለምርት የማብቃት ሥራ መሥራቱን ጠቁመው የፕሮግራሙን ውጤታማነት ማረጋገጥ የሚያስችል የፋይናንስ አቅርቦትን ማጠናከር ከኢትዮጵያ ንግድ ጋር የተፈረመው ስምምነት አንዱ የትኩረት ነጥብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የማደግ አለኝታ ያላቸውን አምራች ኢንተርፕራይዞች የሀገራችንን ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሽግግርን ከማሳካትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችላቸውን አቅም ከማሳደግ አንፃርም ስምምነቱ ጉልህ ሚና እንዳለው ክብርት ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
በውጭ ሀገር በሚፈጠሩ ሥራ ዕድሎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ በያሉበት ሀገር ሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲቆጥቡ፣ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም የቆጠቡትን ገንዘብ ተጠቅመውና ተጨማሪ ብድር አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ብሎም የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል የጋራ ተግባራትም በስምምነቱ ውስጥ መካተታቸውን በፊርማ ሥነሥርአቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገራችን ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ አሻራውን እያኖረ እንደሚገኝ የጠቆሙት ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ባንኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥራ ፈጣሪዎችን ወደ ግባቸው ለማድረስ የሚደርገው ጉዞ አካል ለመሆን ላሳየው ተነሳሽነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ለወቅታዊ ትኩስ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
🌐 Official Website: mols.gov.et
📘 Facebook: https://web.facebook.com/MolsFDRE
📣 Telegram: t.me/fdre_mols
🎵 TikTok: tiktok.com/@mols_official
🐦 Twitter / X: twitter.com/Jobs_ሚኒስቴር
🟢 WhatsApp: whatsapp.com/channel/0029VakCgcYIyPtTbPZtDW1y












