ተወዳዳሪዎቹ ያሳዩት ብቃትና ተወዳዳሪነትና ሴቶች እድል ካገኙ ለሀገር የሚተርፍ ምጡቅ ሃሳብን ማመንጨት እንደሚችሉ ለመረዳት አስችሎናል ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
March 28, 2025

ተወዳዳሪዎቹ ያሳዩት ብቃትና ተወዳዳሪነትና ሴቶች እድል ካገኙ ለሀገር የሚተርፍ ምጡቅ ሃሳብን ማመንጨት እንደሚችሉ ለመረዳት አስችሎናል
ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከእናት ባንክ ፣ ከኢንተርፕርነሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) እና ከተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ (UN women) ጋራ በመተባባር ‹‹ብሩህ-እናት›› በሚል ስያሜ ያዘጋጀው የሴቶች የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
በመርሃግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ተወዳዳሪዎቹ በቆይታቸው በግል ጥረታቸው ያዳበሩትን የፈጠራ ብቃት ወደ ንግድ ሃሳብ መቀየር የሚያስችል ሥልጠና ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
በውድድሩ አስር ቀናት ቆይታ ተወዳዳሪዎቹ ያሰዩት ብቃትና ተወዳዳሪነትና ሴቶች እድል ካገኙ ለሀገር የሚተርፍ ምጡቅ ሃሳብን ማመንጨት እንደሚችሉም አስገንዝቦናል ብለዋል፡፡
በተወዳዳሪዎች የቀረቡት የፈጠራ ሃሳቦች ጥልቀትና ችግር ፈቺነትም ሀገራችን ኢትዮጵያ ፈጠራና ኢኖቬሽንን በማሳደግ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ የያዘችውን ዕቅድ ከማሳካት አንፃርም የሴቶች ሚና ጉልህ መሆኑን ያመላከቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የፈጠራ ሥራዎቻቸው ወደ ቢዝነስ ተቀይረው ለገበያ እንዲበቁና የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት እንዲችሉም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተገቢውን መንግስታዊ ድጋፎች እንዲያገኙ የሚያደረገውን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ክቡር ሚኒስትር ድኤታው አስታውቀዋል፡፡
ብሩህ እናት የቢዝነስ ሃሳብ ውድድር ላይ ለማሳተፍ ከተመዘገቡ 630 ሃሳቦች መካከል ወደ ቡት ካምፕ የሚገቡ 50 ተወዳዳሪዎች በቅድሚያ ተለይተዋል፡፡
በቡት ካምፕ ቆይታቸውም በየደረጃው በተደረገው ውድድር የተለዩ 10 አሸናፊዎች በውድድሩ ማጠቃለያ መርሃግብር ከአንድ መቶ ሺ እስከ 5መቶ ሺብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡



